ቀጥታ፡

በሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት የሲሚንቶ ምርትን ማሳደግ አልታቸለም

አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2010 በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ምርትን ለማሳደግ ዘርፉ የሚጠይቀውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል የአገር ውስጥ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለ ተገለጸ። ሦስተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የሲሚንቶ፣ የኮንክሪትና ኃይል ዓመታዊ ጉባዔ ''የሲሚንቶና ኮንክሪት ዘላቂ ኢንቨስትመንት በምስራቅ አፍሪካ'' በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። ኢትዮጵያ በሲሚንቶ ዘርፍ ከፍተኛ የማምረትና የመጠቀም አቅም ቢኖራትም ዘርፉ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂዎች የሚያንቀሳቅስ የሰው ኃይል ችግር እንዳለባት በጉባዔው ላይ ተጠቅሷል። የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ኃይሌ አሰግዴ እንዳሉት በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች 75 በመቶ የሚሆኑት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ሲሆን ፋብሪካዎቹ የሚንቀሳቀሱት በውጭ አገር ባለሙያዎች ነው። በአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሲሚንቶ ምርት ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚያሰለጥኑት የሰው ኃይል እንደሌለም ተናግረዋል። የመለዋወጫ ዕቃዎች ከውጭ የሚገቡ በመሆኑ በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፋብሪካዎችን ምርት እስከ ማቆም ያደረሰ ተፅዕኖ እንደነበረው አስታውሰዋል። የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሀላላ በሲሚንቶ ምርት በኩል የቴክኖሎጂ ችግር እንደሌለ ጠቁመው የኢንዱስትሪዎችን መስፋፋት ተከትሎ ቴክኖሎጂዎቹን የሚያንቀሳቅስ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለ ተናግረዋል። የሰው ኃይል እጥረቱን ለመቀነስ ኢትዮጵያውያን በፋብሪካዎቹ ውስጥ ከሚሰሩ የውጭ አገር ባለሙያዎች ጋር አብረው የሚሰሩበትና የእውቀት ሽግግር የሚያደርጉበት የስልጠና መርሐ ግብር መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በስምንት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ስልጠና የሚሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተመርጠው በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በደረጃ አንድ፣ ሁለትና ሦስት ለማሰልጠን የስልጠና መርሐ ግብር ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደተቃለለ የገለጹት አቶ ሳሙኤል የኃይል መቆራረጥን ከማስቀረት አኳያ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ፋብሪካዎች ከዋና ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል እንዲያገኙ ቢደረግም በኃይል ተሸካሚ ገመዶች አቅም ማነስ ምክንያት መቆራረጥ ይታያል ብለዋል። በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሽፈራው ፈይሳ እንዳሉት የዘርፉን የሰው ኃይል ለማፍራት ዩኒቨርሲቲው በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ማዕከል አቋቁሟል። ማዕከሉ አገራዊ የሲሚንቶ ፍላጎትን ለማሳካት የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሰው ኃይል ስልጠና ላይ ይሰራል ብለዋል። እንዲሁም ማዕከሉ የኢትዮጵያ ሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ማሰልጠኛ ተቋም በመሆኑ ኢንዱስትሪው አካባቢያዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም  በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚሰራም ገልጸዋል። በጉባዔው ላይ ከህንድ፣ ከግብጽና ከኬንያ የመጡ የሲሚንቶ ፋብሪካ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ልምዳቸውን ያካፍላሉ ተብሎም ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አስራ ስድስት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን በዓመት በአማካኝ 17 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንዳላቸውም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም