ኤጀንሲዎች የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅን በትክክል ተግባራዊ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲዎች የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅን በትክክል ተግባራዊ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 02/2013 (ኢዜአ )የአገር ውስጥ የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅን ተግባራዊ በማድረግ በሰራተኞች ላይ እየፈጸሙ ያለውን የመብት ጥሰት እንዲያርሙ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
በምክር ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ እና የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴዎች የአገር ውስጥ የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ላይ ዛሬ ተወያይተዋል፡፡
በዚህም በዋናነት ኮሜርሻል ኖሚኒስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኤጀንሲ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ባደረጉት የመስክ ምልከታ ሪፖርት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተዋል።
ቋሚ ኮሚቴዎች በምልከታቸው በኮሜርሻል ኖሚኒስ አማካኝነት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በድጋፍ ሰጪነት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታችው እየተጣሰ መሆኑን የሰራተኛ ማህበሩ በዝርዝር አስረድቷል ብለዋል።
በባንኩ በድጋፍ ሰጪነት በኮሜርሻል ኖሚኒስ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን በተመለከተ ማህበሩ እየደረሰ ያለውን በደል በዝርዝር አቅርበዋል።
ከተዘረዘሩት ውስጥ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ዓ.ም ተከትሎ የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሃገር ውሰጥ የስራ ስምሪት አገልግሎት ስለሚሰጥበት ሁኔታ ለመወሰን የወጣው መመሪያ ላይ ስለደሞዝ አከፋፈል የተደነገገው 20/80 ተግባራዊ እያደረገ አይደለም።
መመሪያው ከሰራተኞች ደሞዝ 20 በመቶውን ኤጀንሲ 80 በመቶ ሰራተኛ እንዲወስዱ ቢያስቀምጥም ኤጀንሲው እስከ 40 በመቶ እየወሰደ እንደሚገኝ በምልከታው ተረጋግጧል ተብሏል።
የአመት እረፍት፣ ቋሚ ሰራተኛ የመሆኛ ጊዜ ገደብ፣ የህክምና እና ሌሎች በአዋጁ ላይ የተደነገጉ የሰራተኛ መብቶች እየተጣሱ መሆኑንም ቋሚ ኮሚቴዎቹ አረጋግጠናል ብለዋል።
በሰራተኛው ከሚከፈል የጡረታ ሰባት በመቶ መዋጮ በተጨማሪ ድርጅቱ መክፈል የነበረበትን 11 በመቶ የጡረታ መዋጮ ሰራተኞች እንዲከፍሉ እየተደረገ ሲሆን በተጨማሪም በማያውቁት ምክንያት ከደመወዛቸው 1 ሺህ 937 ብር ይቀነስባቸዋል።
የተዘረዘሩት የመብት ጥሰቶች በህጋዊ ሽፋን ህገ-ወጥ ተግባራት እየተከናወነ ለመሆኑ ማሳያ መሆናቸውን ሪፖርቱ አስቀምጧል።
በተነሱ ችግሮች ላይ ምላሽ የሰጡት የኮሜርሻል ኖሚኒስ ስራ አስፈጻሚ ኮማንደር ጥላሁን ታደሰ በሪፖርቱ የቀረቡ ችግሮች የተጋነኑ፣ የሃላፊዎችን ሃሳብ ያላካተቱና ሚዛናዊነት የጎደላቸው እንደሆኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ተቋሙ በኮሜርሻል ኖሚኒስ አማካኝነት የቀጠራቸው ቋሚና ጊዜአዊ ሰራተኞች ላይ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት ሚዛናዊነት የጎደለውና ችግሮች ጎልተው የወጡበት ነው ብለዋል።
ባንኩ በኤጀንሲ አማካኝነት እየፈጸመ ያለውን የሰራተኛ ቅጥር አካሄድ በቀጣይ በአሰራርና በጥናት በመለየት እንደሚተገብር ገልጸዋል።
ሃላፊዎች ይህን ይበሉ እንጂ በምልከታው የተሳተፉ የምክር ቤት አባላት በምልከታው ወቅት የታየው በሪፖርቱ ከቀረበው የከፋ መሆኑና የሚመለከታቸውን አካላት በችግሮቹ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አዋጁ ከኤጀንሲዎች ጋር ውይይት ተደርጎበት የወጣ በመሆኑ የመተግበር ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኤጀንሲዎች ህግና ስርአትን ተከትሎ ከመስራት ይልቅ 20/80 ህጉ ተግባራዊ እንዳይሆን በፍርድ ቤት መመሪያውን በማሳገድ ተግባራዊ እንዳይሆን እያደረጉ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
በምክር ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ የተወሰኑ ኤጀንሲዎች ህግ አክብረው እየሰሩ ቢሆንም አብዛኛው ሰራተኛና አሰሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሰራተኞች ላይ እየፈጸሙ ያሉትን ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር እንዲያርሙ አሳስበዋል።
መመሪያውን በፍርድ ቤት ማሳገድ መፍትሄ ባለመሆኑ ችግር ካለበት ለማሻሻል መወያየት መፍትሄ እንደሆነ አስረድተዋል።
በምክር ቤቱ የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ጫኔ ሽመካ በሰራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና እንዲቆምና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል።