በአዲስ አበባና በአንድ አንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባና በአንድ አንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ
ግንቦት 2/2013(ኢዜአ) በአዲስ አበባና በአንድ አንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤በአዲስ አበባና በአንድ አንድ የኦሮሚያ ከተሞች ሁከት፤ሽብርና ትርምስ በመፍጠር ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ የውጭ እና የውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚደገፉ የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሴራ ወጥነው ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳሉ በጋራ ግብረ ኃይሉ በተደረገባቸው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ይሄንን እኩይ የጥፋት ሴራ ለመፈጸም ከውጭ በተለያዩ አካላት በሚደረግላቸው የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎች ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት ከከባድ እስከ ቀላል የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ከመሰል ጥይቶች፣ ቦንቦችና ተቀጣጣይ ቁሶች ጋር ለጥቃት ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጇቸው ቢሆንም፤ የታቀደውን የጥፋት ተልዕኮ ማክሸፍ መቻሉን መግለጫው አትቷል።
ለሸብርተኞቹ በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርትና በሌሎችም አካባቢዎች ጭምር የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች በህገወጥ መንገድ ሊተላለፉ እንደነበር የጠቆመው መግለጫው ፤በተደረገ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻም ለጥፋት ተልዕኮ መፈፀሚያቸው ሊጠቀሙበት የነበረ ከ305 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እና ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ መያዙን አስታውቋል፡፡
መግለጫው እንዳብራራው፤ይሄንን የጥፋት ተግባር ለመፈፀም ቀደም ሲል ትግራይ ድረስ ታጣቂዎቹን መልምሎ በመላክ ከሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ በንፁሃን ዜጎች ላይ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን ሲፈፅም የቆየው የአሸባሪው የሸኔ ቡድን፤ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያገኝ እንደቆየና፤በቡድኑ ላይ የመንግስት ፀጥታ አካላት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰዱበት ባለው ተከታታይ እርምጃ እየተዳከመና ከባድ ኪሳራ እያጋጠመው መጥቷል።
በዚህም ምክንያት መሰረተ ልማቶችን እንዲያወድሙ እንዲሁም በታዋቂ ሰዎች፤በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና በዜጎች ላይ በተደራጀና በተጠና መንገድ ግድያ እንዲፈፀሙ “አባ ቶርቤ” በሚል የሰየማቸውን የከተማ ክንፍ አሸባሪዎች ወደ ተለያዩ ከተሞች አሰማርቶ ነበር ብሏል፡፡
ለእነዚህ የሽብር ቡድኖች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን፤ቦንቦችን፣ ለፍንዳት ስራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሶችን እንዲሁም ሰነዶችን በስውር ለመስጠት ሲያጓጉዙ የነበሩ በርካታ የቡድኑ ተጠርጣሪ አባላት መያዛቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ከተጠርጣሪዎች መካከልም አብዲሣ ጣፋ ቆጮልቴ እና ኤብሣ ተረፋ ቶኮሣ የተባሉት ግለሰቦች ከአማራ ክልል ሁመራ አካባቢ በኮድ ሁለት የታርጋ ቁጥር A70977-አአ ሚኒባስ መኪና የውስጥ አካል የተለያዩ የጦር መሳሪዎችንና ጥይቶችን ሰግስገውና ደብቀው መዳረሻቸውን ምዕራብ ኦሮሚያ አድርገው በደሴ በኩል አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ ለገጣፎ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።
በተመሳሳይ አርጆ አለማየሁ ዋቆ የተባለች የሸኔ ቡድን አባል ሶላር የተገጠመላቸው ዓለምአቀፍ የሳተላይት ስልኮችን በሞያሌ በኩል በማስገባት ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በድብቅ ለማሰራጨት ስትሞክር ቡራዩ ከታ ላይ እጅ ከፍንጅ መያዟን የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ ጠቁሟል።
ራቢራ ዊርቱ ሞሲሳ፣ደረጄ ዱጋሳ ሆርዶፋ እና ወንደሰን መግራ ታደሰ የተባሉ ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላትም ተጨማሪ የሳተላይት ስልኮችን ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት ሲሞክሩ፤በነበረው ሚስጥራዊ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተጠቅሷል፡፡
ሽብርተኛው የሸኔ ቡድን በተደራጀና በተጠና መንገድ ግድያ እንዲፈፅሙ አዲስ አበባና በአንድ አንድ የኦሮሚያ ከተሞች ያሰማራቸው “የአባ ቶርቤ” ቡድን አባላት ተመሳስለው ጥቃት የሚፈፅሙባቸው የመከላከያ ሰራዊት የቀድሞው ደንብ ልብሶችንና እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንም ጭምር በድብቅ ሲጓጓዙ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አትቷል።
አበራ ሙለታ፣ለሊሳ አዳሙ፣ አበራ ጌታ፣ሙሌ ስዩሜና አብርሃም አቡ የተባሉ የቡድኑ አባላትና የድርጊቱ ተዋናዮች እንዲሁም አሽከርካሪውና ረዳቱም መያዛቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡ 2 የሽብር ቡድኑ በጅማ ከተማ ጥቃት ለመፈጸም ስምሪት የሰጣቸው፤ኢያሱ ለማ፣ካሊድ ሰይድ፣አብደላ አባ በላይ፣ሰይፉ በላይ እና ነጋሳ ኬኔሳ የተባሉ ተጠርጣሪዎችም ከታጠቋቸው የእጅ ቦንቦችና እና ሽጉጦች እንዲሁም ከሌሎች የጥፋት ተልዕኮ መፈጸሚያ ቁሶች ጋር መያዛቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩና ለአሸባሪው የሸኔ ቡድን የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎች የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ያመለከተው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ፤ እነርሱም ጀምበሩና አበበ አሜሪካ፤ ገመቹ ፣አብደላ እና ተርፋ አውስትራሊያ ዱጋሳ ኖርዌይ እንዲሁም ቶለሸ ታምሩ ወይንም ገቢሴ፣ገመቹ አቦዬ፣ለማ ረጋሳ ወይንም ቢቂላ እና ጃራ ቱለማ ኬንያ የሚኖሩ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
እነዚህን የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ እየደገፉ ያሉትን በድምሩ 15 ተጠርጣሪዎችን ማንነትን በማጣራትም ለህግ ለማቅረብ ከወዳጅ ሀገራት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በሀገር ውስጥ እስካሁን የቡድኑን የሽብር እንቅስቃሴ ለመግታት በተወሰደው እርምጃ የከተማ ሴል አባላትን ጨምሮ 71 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል፡፡
መግለጫው አክሎም፤ ለሽብር ቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የ80 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥ የተደረገ መሆኑን በማሳወቅ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቡድኑ ዋና ዋና የገንዘብ አስተላላፊ ተብለው የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ መዋላቸውና ሌሎችንም በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ከአሸባሪው የሸኔ ቡድንና ከሌሎች ፀረ-ሰላም ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረው የሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የፈፀመውን የሀገር ክህደት ወንጀል ተከትሎ፤መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ የቡድኑ ቁልፍ አመራሮች እርምጃ ሲወሰድባቸውና ገሚሶች ደግሞ እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲሰጡ፤ ጥቂት የታጠቁ የቡድኑ ሃይሎች በተንጠባጠበ መልኩ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱ የገለፀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ቡድኑ የተወሰደበትን ተከታታይ እርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ ‹‹ክብሪት›› የሚል መጠሪያ የሰጠውን ገዳይ ቡድን በክልሉ ዋና ዋና ከተሞችና በአዲስ አበባም ጭምር ለማሰማራት መሞከሩን አትቷል፡፡
በአሜሪካ የሚኖሩ ጀነራል ፍስሃ ማንጁስ ፣ካህሳይና ወዲ ምጉላት የተባሉ ግለሰቦች፤በሆላንድ የሚኖሩ ተክላይ እና አታክልቲ፤እንግሊዝ የሚኖረው ታከለ፤ስዊድንና ደቡብ ሱዳን የሚኖሩት ተስፋይ ንጉስና ሰይፈ አምባዬ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ሽብርተኛውን የሕወሓት ቡድን በገንዘብ የሚደግፉ መሆናቸው በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን የገለፀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ግለሰቦቹን በህግ ተጠያቂ የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስታውቋል፡፡በሀገር ውስጥ ሆነው ለቡድኑ የገንዘብና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ 32 የቡድኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አመልክቷል፡፡
በቡድኑ ለሽብር ድርጊቱ ሊውሉ የነበሩ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች፣የሬድዮ መገናኛዎች እና ሌሎች ተቀጣጣይ ቁሶችም መያዛቸውን ጠቁሟል፡፡
እነዚህ ሽብርተኛ ቡድኖች ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት ሀገሪቱን ወደ ሽብርና ትርምስ ውስጥ በማስገባት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ሴራ ወጥነው ለመንቀሳቀስ እየሞከሩ ቢሆንም፤ የደህንነትና የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በቅንጅት በመስራት ሴራቸውን አስቀድሞ ማክሸፍ መቻሉን የጋራ ግብረ ሃይሉ ገልጿል።
የሸኔና የህወሓት ሽብርተኛ ቡድን አባላት በመንግስት ጸጥታ ሀይሎች እየተወሰደባቸው ባለው ተከታታይ እርምጃ፤በርካታ የቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንና መያዛቸውን እንዲሁም ለሽብር ተልዕኳቸው የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣የእጅ ቦንቦች፣ለፍንዳታ ስራ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሶችና ሰነዶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል። ይህን ተከትሎም የሽብር ቡድኖቹ ከፍተኛ ኪሳራና የስነልቦና ጫና ውስጥ መግባታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
የጋራ ግብረ ኃይሉ የውስጥና የውጭ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተው ሀገሪቱን ወደ ለየለት ትርምስ ለመክተትና ለማፍረስ እየሰሩ ቢሆንም፤ በርካታ ሴራዎችን አስቀድሞ በማወቅ ማክሸፍ መቻሉንና የትኛውም ሴራ ከመንግስት እንዲሁም ከደህንነትና ጸጥታ አካላት እይታ የተሰወረ አለመሆኑንም ገልጿል።
3 ሀገራችን ኢትዮጵያ በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች ባለችበት በአሁኑ ጊዜ በአንድ አንድ የውጭ ሀይሎች በቀጥታ ከሚደርስባት ጫና ባሻገር፤ ከተመቻቸው በጥቂት ተላላኪዎቻቸው የሸኔና የህወሓት ሽብርተኛ ቡድኖች ጥቃት በመሰንዘር ካልተመቻቸው በህቡዕ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ሀገሪቱ ወደትርምስ እንድትገባ የተለያዩ እኩይ ሴራዎች እየተጠነሰሱ መሆናቸውን ህዝባችን ሊገነዘብ ይገባል ብሏል የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው፡፡
በመሆኑም ህዝባችን፤ሰላሙንና ደህንነቱን ለመጠበቅ እንዲሁም የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ሴራዎቹን በማክሸፍ ለአፍታም አይን በማያስከድን ስራ ላይ የተሰማሩ የመረጃና ደህንነት እንዲሁም የጸጥታ ተቋማትና አካላትን የተቀናጀ እንቅስቃሴ በመደገፍ እያደረገ ላለው ትብብር የጋራ ግብረ ኃይሉ ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
ተመሳሳይ ሀገር የማፍረስ እኩይ ሴራዎችን በማክሸፍ በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በቀጣይ ለህዝቡ የማሳወቅ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን መግለጫው አረጋግጧል፡፡
(የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እና የኦሮሚያ ፀጥታ ተቋማት)