እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላትን ትብብር አጠናክራ መቀጠል ትፈልጋለች -በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላትን ትብብር አጠናክራ መቀጠል ትፈልጋለች -በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 02 /2013 (ኢዜአ) እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የአገሪቱ አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ የሁለቱ አገራት የቱሪዝምና የልማት የትብብር መስኮችን በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
አምባሳደር አለልኝ አድማሱ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ እስራኤልና ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው።
ይህም ታሪካዊ የአገራቱ ወዳጅነት በተለያዩ መንግሥታት ዘመን የተለያዩ የእድገት ደረጃዎችን በማለፍ በሌሎችም የልማት ዘርፎች ላይ ትብብሩ መጠናከሩን ገልጸዋል።
ያም ሆኖ ግንኙነቱ አሁን ካለበት ደረጃ ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸው፤ እርሳቸውም በቆይታቸው ይህንን ወዳጅነት ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ ነው አምባሳደሩ የጠቆሙት።
እስራኤል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላት አቅምና ልምድ ከፍተኛ እንደሆነና ይህንንም ዘመናዊ እውቀት ለኢትዮጵያ ለማጋራት ይሰራል ብለዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብርና ልማት ሥራዎች፤ አርቴፊሻል ዝናብ ማዝነብን ጨምሮ ሳይንሳዊ የሆኑ የግብርና ሥራዎችን ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የልማት ሥራዎቿን ለማቀላጠፍ የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትእስራኤል የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የሁለቱን አገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ አሁን ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ትኩረት እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት።
በሌላ በኩል በእየሩሳሌም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዴር ሱልጣን ገዳም ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
"እስራኤል ሦስቱ የአብርሃም ኃይማኖቶች ተቻችሎ የሚኖሩባት አገር ናት" ያሉት አምባሳደሩ ውዝግቡ በዚህ አግባብ እልባት እንደሚሰጠው አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያና እስራኤል ከ3 ሺ ዓመታት በላይ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን እ.ኤ.አ ከ1960 ዎቹ ጀምሮ ደግሞ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ጀምረዋል።