የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሂደት በኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ ግልጽ የአሰራር ሂደት የታየበት ነው- ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ - ኢዜአ አማርኛ
የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሂደት በኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ ግልጽ የአሰራር ሂደት የታየበት ነው- ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 02/2013 (ኢዜአ ) የስድስተኛው አጠቃላይ የምርጫ ሂደት በኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ ግልጽ የአሰራር ሂደት የታየበት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገለጹ።
ሰብሳቢዋ በቅርቡ አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሬይ ፌልትማን ለጻፉት ደብዳቤ በሰጡት ምላሽ ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መወሰዳቸውንም ጠቁመዋል።
ቤን ካርዲን፣ቲም ኬይን፣ጃኪ ሮሰን፣ኮሪ ቡከርና ኢድ ማርኬይ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ለጄፍሬይ ፌልትማን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በጻፉት ደብዳቤ ላይ “ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አላሟላም” ሲሉ ገልጸዋል።
የምርጫ ሂደቱ ነጻነት፣ፍትሐዊነትና ግልጸኝነት የሚሉትን የምርጫ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች የሚያሟላ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
“በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ እንደማይሳተፉ አሳውቀዋል ምርጫው ተአማኒ ነው የሚል እምነት የለም” ብለዋል ሴናተሮቹ በጻፉት ደብዳቤ።
“የሕዝቡን እምነት የሚጨምሩ የማሻሻያ እርምጃዎች ሳይወሰዱ ምርጫው ቢካሄድ አሁን በኢትዮጵያ ያሉ የማንነትና የፖለቲካ ውጥረቶች ወደ ከፋ ግጭት ያመራሉ” ሲሉ ሴናተሮቹ ገልጸው ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሴናተሮቹ ምላሽ በሰጡበት ደብዳቤ ላይ እንደገለጹት በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ያሉ ምልከታዎች ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር መመልከት ይገባል።
ምርጫ ቦርድ ቀጣዩ ምርጫ ከኢትዮጵያ ሕጋዊ ማዕቀፍና ዓለም አቀፍ መስፈርተኞች ያሟሉ እንዲሆኑ እየሰራ ነው ብለዋል።
ይሁንና የሕዝብ ብዛት፣በሁሉም ደረጃ ያሉ የልማት ጉድለቶች፣የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በእድገት ላይ የሚገኝ መሆኑ እንዲሁም የፖለቲካና የደህንነት ሁኔታው በምርጫ ሂደቱ ላይ ጉድለቶች እንዲኖር ማድረጉ የሚጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
የተጠቀሱት ሁኔታዎች የሕዝቡ ድምጽ የመስጠት አቅምና አለመግባባቶች ለመፍታት በሁሉም ደረጃ የተዘረጉ የአሰራር ስርዓቶች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ነው ወይዘሪት ብርቱካን የገለጹት።
ይሁንና የምርጫ ባለድርሻ አካላት ከምርጫው የሚጠበቁት ነገር አሁን እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ተናግረዋል።
የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ አስተዳደር በኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ ግልጽ የአሰራር ሂደት የታየበት ነው ብለዋል።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ከተገለጸበት ጊዜ አንስቶ ከምርጫ ባለድርሻ አካላት ጋር ከ50 በላይ የምክክር መድረኮች መካሄዳቸውን አመልክተዋል።
የምክክር መድረኮቹ የምርጫ ባለድርሻ አካላት በምርጫ ሂደቱ ላይ ያሉ ፈተናዎችን እንዲረዱና የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲወስዱ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።
በቦርዱ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ምርጫ የተመለከቱ መረጃዎችን በመደበኛነት ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ነው በደብዳቤው ላይ የገለጹት።
በምርጫ ዝግጅቱ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ግልጽነትን የተከተሉ መሆናቸውን ነው ወይዘሪት ብርቱካን ያስረዱት።
ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎችን መወሰዱንም ተናግረዋል።
የባለድርሻ አካላትን ግብረ መልስ በምርጫ መመሪያዎች ውስጥ ማካተት አዳዲስ የድምጽ መስጫ ሳጥኖች፣ለምርጫ ስራ የሚያስፈልጉ ስክሪኖች፣የማይጠፉ ቀለሞች፣የድምጽ መስጫና ሌሎች የምርጫ ቁሳቁሶች ግዢ መፈጸሙን አመልክተዋል።
የምርጫ ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያደርጉ ገጽታዎች ማዘጋጀት፣የተዘረጉ አሰራሮችና የምርጫ ሂደት ቁጥጥርና ክትትል ለማጠናከር ስልጠናዎች መሰጠታቸው ነው በደብዳቤው ላይ የሰፈረው።
የተወሰዱና ከዚህም በኋላ የሚወሰዱ እርምጃዎች የአሁኑን ምርጫ ከዚህ በፊት ከተካሄዱት ምርጫዎች አንጻር የተሻለ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚታመን ገልጸዋል።
በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት በምርጫ ሂደቱ ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑና የሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች በተቻለ አቅምና ፍጥነት ለመፍታት ቦርዱ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በምርጫ ሂደቱ መሳተፍ ምርጫው ግልጸኝነት ለማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል ወይዘሪት ብርቱካን።
አሜሪካ ለስድስተኛው ምርጫ እያደረገች ላለው የቴክኒክና የቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው የምርጫ ሂደቱ በቅርበት መከታተሏንና መታዘቧን እንድትቀጠል ጠይቀዋል።
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲሁም ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ይካሄዳል።