ቀጥታ፡

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ከኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣  ግንቦት 02/2013 (ኢዜአ) የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሬይ ፌልትማን ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና ከህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ጋር ውይይት አደረጉ።

በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ልዩ መልዕክተኛው ትናንት አመሻሹ ላይ ነው ኢትዮጵያ የገቡት።

ጄፍሬይ ፌልትማን ከኢትዮጵያ በፊት በግብጽ፣ በሱዳን እና ኤርትራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በጉብኝታቸው ከአገራቱ መሪዎች ጋር ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል።

ዛሬ ደግሞ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ያላትን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት አቋምና አጠቃላይ የሶስትዮሽ ድርድሩን ሁኔታ በሚመለከት ገለጻ አድርገውላቸዋል።

ልዩ መልዕክተኛው ግድቡን በሚመለከት ላነሱት ጥያቄ ማብራሪያ እንደተሰጣቸውም ነው የተገለጸው።

በውይይቱ የተሳተፉት የህዳሴ ግድብ ተደራደሪ ቡድን አባል ኢንጂነር ጌዴዮን አስፋው ልዩ መልእክተኛው በሱዳንና ግብጽ በነበራቸው ጉብኝት ግድቡን በሚመለከት ከአገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በዛሬው ውይይትም ግድቡን በሚመለከትም ከኢትዮጵያ በኩል ያለውን ምልከታ በሚመለከት ዝርዝር ገለጻ ተደርጎላቸዋል ነው ያሉት።

ልዩ መልዕክተኛው የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በሚመለከት ላነሱት ጥያቄ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ገልጸው፤ በዚህም ኢትዮጵያ በመጪው የክረምት ወቅት ውሃ እንደምትሞላ ገልጻለች ብለዋል።

የውሃ ሙሌቱም የሶስቱም አገራት ኤክስፐርቶች ከዚህ ቀደም ባስቀመጡት አግባብ እንደሚከናወን ነው ያስረዱት።

በዓለም ላይ በተገነቡ በርካታ ግድቦች የተነሱ አለመግባባቶች በውይይት መፈታታቸውን አስታውሰው፤ የህዳሴ ግድብ ላይ የሚነሳው ጉዳይም በውይይትና ድርድር እንጂ በግጭት መፈታት እንደማይችል ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚከናወነው የሶስትዮሽ ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጽኑ አቋም እንዳላት ሚኒስትሩ መናገራቸውንም ገልጸዋል።

የታዛቢዎች ሚናን በሚመለከት ገለጻ እንደተደረገላቸውም ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው አውስተዋል።

ታዛቢዎች ሶስቱ አገሮች በሚስማሙበት አግባብ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የየትኛውንም አገር መብት በሚጥስ መልኩ ጣልቃ መግባት እንደማይችሉም ነው ያነሱት።

ልዩ መልእክተኛው በአፍሪካ አገራት ከሚኖራቸው ቆይታ በተጨማሪ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከሰብአዊ እርዳታ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጄፍሬይ ፌልትማን  ከሶስት ሳምንት በፊት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም