በምርጫ ሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግስት አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫ ሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግስት አስታወቀ
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2013/ኢዜአ/ በምርጫ ሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግስት አስታወቀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር በምርጫ እንቅስቃሴው ላይ እንከን መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መንግስት የምርጫውን ሰላምና ጸጥታ ማረጋገጥ ዋንኛ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ሲጠይቅ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር የምርጫ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማጓጓዝ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ለመስራት እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም መንግስት ከቦርዱ ጋር በመነጋገር የጸጥታ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በጋራ እየሰሩ በመሆኑን ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።
በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ባልተጀመረባቸው አካበቢዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ዜጎች በምርጫው ላይ ያለፀጥታ ስጋት ተሳትፎ እንዲያደርጉ መንግስት ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ስራውን በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2013 ዓ.ም ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ መንግስት አገራዊ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድም የፖሊስና ደህንነት ተቋማትን ያቀፈ ብሔራዊ የደህንነት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በቅድመ ምርጫ ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በምርጫ ዕለትና ከምርጫው በኋላ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን የመለየትና የመተንተን ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ተቋማት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ቢታዘቡ መልካም እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ቢቂላ የታዛቢዎቹ መቅረት በምርጫው ሂደት ላይ የሚያሳድረው ጉዳት እንደማይኖር ተናግረዋል።
ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ሌላ የውጭ አካል አይደለምም ነው ያሉት።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች ልዩ እቅድ እና ዝግጅት በማድረግ ከየክልሎቹ የጸጥታ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
በዚህም የአስፈጻሚዎች ስልጠና እና የቁሳቁስ ስርጭት የተከናወነ እንደሆነና በተጨማሪም የመራጮች ምዝገባ (4ቱ ወለጋ ዞኖች (24 ምርጫ ክልሎች)፣ ካማሽ (4 ምርጫ ክልሎች) እና አማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን (3 ምርጫ ክልሎች) ከሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 13/2013 በልዩ ሁኔታ ምዝገባ እያከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቋል።
6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ የፊታችን ግንቦት 28 ሲካሄድ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ደግሞ ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።