ቀጥታ፡

ሰራተኞች እያሳዩት ያለው መዘናጋት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው----የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን

አዲስ አበባ፣  ግንቦት 02/2013(ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥንቃቄዎች ላይ ሰራተኞች እያሳዩት ያለው መዘናጋት ወረርሽኙ እንዲስፋፋ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ገለጸ።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ቢቀጥልም በሰራተኞች እንዲሁም አጠቃላይ በማህበረሰቡ ዘንድ መዘናጋት ይስተዋላል።

በመሆኑም የወረርሽኙ መስፋፋትና በቫይረሱ የሚያዙ ሰራተኞች እየተበራከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከሰራተኞች ባሻገር ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከል ከዚህ ቀደም ያደርጉ የነበሩት ጥንቃቄ አሁን ላይ ተቀዛቅዞ ይገኛልም ብለዋል።

በተለይ በትራንስፖርት አገልግሎት፣ በካፌና ሬስቶራንቶች፣ በመዝናኛ ስፍራዎችና በሌሎችም አካባቢዎች የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገው ጥንቃቄ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም በስራ ቦታ በፋብሪካዎች ላይ የሚከናወኑ ስራዎች ለንክኪ የተጋለጡ በመሆናቸው በስራ አካባቢዎቻቸው የሰዎችን ንክኪ በመቀነስ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን በአግባቡ በመጠቀምና ርቀትን በመጠበቅ መስራት ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል ክትባቶች እየተሰጡ ቢሆንም ጎን ለጎን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መግባቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በአጠቃላይ ከ262 ሺህ በላይ ዜጎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ከ3 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም