ቀጥታ፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ 31 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 02/2013(ኢዜአ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ 31 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።

የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚን ዎሃብረቢ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አብዱል ካማራ ዛሬ ተፈራርመዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ያደረገው የ31 ሚሊዮን ዶላር /1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር/ ድጋፉ የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያ የህጻናትን ስር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትንና የመቀንጨር  ችግር ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡

የፋይናንስ እገዛው በሰቆጣ ቃልኪዳን መመሪያ ፕሮግራም መሰረት በአማራና በትግራይ በሚገኙና የመቀንጨር ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው የተመረጡ የክልሎቹ ወረዳዎች ይውላል ተብሏል፡፡

በዚህም ከተመጣጠነ ምግብ ጋር በተያያዘ በአካባቢዎች የሚከናወኑ ተግባራትንና ለስኬቱ አጋዥ የሆኑ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ፍላጎትን ለማሟላት ይረዳል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የህፃናትን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት በዘለቄታው ለመፍታት ያጸደቀችውን የሰቆጣ ቃል ኪዳን እውን ለማድረግ እንደሚያግዝም ሚኒስቴር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን በመታገዝ የህጻናትንና የነፍሰጡር እናቶችን አመጋገብ በማሻሻል በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቧን በመጥቀስ ድጋፉ የበለጠ ስራ ለማከናወን አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ድጋፉ በእናቶችና ህጻናት አመጋገብ ዙሪያ እውቀት እና አመለካከትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች የሚከናወኑበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የአንድ አገርን የልማት ጉዞ በእጅጉ እንደሚያደናቅፍ በመግለጽ ድጋፉ ኢትዮጵያ የምግብና የተመጣጠነ አመጋገብ ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ የያዘችውን ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ የሚያከናውናቸውን የተለያዩ የልማት ስራዎች ለማገዝ ለሚያደርገው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አብዱል ካማራ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የህፃናት የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው ለዚህም ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት የህጻናትና እናቶች ስርአተ ምግብ ለማሻሻልና የህፃናት የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የህጻናት የመቀንጨር ችግርን እኤአ እስከ  2030 ለማጥፋት አቅዳ እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም የአፍሪካ ልማት ባንክ በአፍሪካ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያገዘ መሆኑን ገልጸው ይህን መሰል ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም