ቀጥታ፡

ከተማ አስተዳደሩ ትናንት ለተፈጠረው የአደባባይ የኢፍጣር መርሐግብር መስተጓጎል ይቅርታ ጠይቋል

ግንቦት 02፤2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትናንት ለተፈጠረው የአደባባይ የኢፍጣር መርሐግብር መስተጓጎል ይቅርታ ጠይቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "ትናንት ለተፈጠረው ነገር በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብለዋል።''የኢትዮጵያ አደባባዮች የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው'' ያሉት ምክትል ከንቲባዋ አንድ ማዕድ በጋራ የተቋደሰ ህዝብ የኔ፣ የኔ በሚል በአንድ አደባባይ አይጣላም'' ሲሉ ገልጸዋል፡፡

''መርሐግብሩ የተስተጓጎለው ወቅታዊ የደህንነት እና የጸጥታ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የቦታው ስፋት እና ርዝመት ውስን እንዲሆን ባቀረብነው ሀሳብ አዘጋጅ ኮሚቴው ባለማመኑ ብቻ መሆኑ ግልጽ እንዲሆን እንፈልጋለን" ብለዋል።

ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የትናንት ምሽቱ የጸጥታ አካላት እንቅስቃሴም የሁሉም ነዋሪዎች ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ ያለመ እንጂ በፍፁም የኢፍጣር ክልከላ አለመሆኑን ገልፀዋል።

በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ሌሎች የኢፍጣር መርሐግብሮች መካሄዳቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።"ይሁን እንጂ አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው አካላት ይህን ጉዳይ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ በማህበራዊ ሚዲያ ሊያራግቡት ሞክረዋል" ነው ያሉት።

አክለውም ሙስሊሙ ማህበረሰብ በተፈጠረው ሁኔታ የተሰማውን ቅሬታ የገለጸበት መንገድ ጨዋነት የተሞላበት እና ሰላማዊ እንደነበር እና ይህም የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም