በስኬት እየተጠናቀቁ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሚገጥሙንን ችግሮች በድል እንደምንወጣ አመላካቾች ናቸው - አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
በስኬት እየተጠናቀቁ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሚገጥሙንን ችግሮች በድል እንደምንወጣ አመላካቾች ናቸው - አቶ ደመቀ መኮንን
ግንቦት 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) "በስኬት እየተጠናቀቁ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሚገጥሙንን ሀገራዊ ችግሮች በድል እንደምንወጣ አመላካቾች ናቸው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ በ450 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን ዘመናዊ የደረጃዎች አካዳሚ በመረቁበት ወቅት ነው።
አቶ ደመቀ በንግግራቸው "ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል በመሻገር የጀመረችውን ለውጥ ከማስቀጠል የሚያቆማት የለም" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በስኬት ተከናውነው እየተጠናቀቁ መሆኑን አንስተው፤ "ይህም ኢትዮጵያ የገጠሟት ፈተናዎች ሳይበግሯት በድል ወደ ተሻለ ምእራፍ እንደምትሻገር ያመላክታል" ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትናንት የተመረቀውን የሞጆ-መቂ-ባቱ የፍጥነት መንገድ ግንባታን ለአብነት አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው የደረጃዎች አካዳሚ የኢትዮጵያ ምርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ከዝቅተኛ እስከ ውስብስብ ቴክኖሎጂዎች የሚጠይቁ የስራ መስኮች በጥራትና ደረጃዎች በመታገዝ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው "አካዳሚው የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴን እየቀየረ ባለው የዲጂታል ኢንዱስትሪ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያግዛል" ብለዋል።
አካዳሚው ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጠቀሜታ እንደሚኖረው የጠቀሱት አቶ መላኩ፤ የሀገራት እድገት የሚወሰነው ለቴክኖሎጂ ባላቸው ቅርበትና ባላቸው የተማረ የሰው ሃይል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ ተጨማሪ አካዳሚ እየተገነባ መሆኑን ገልጸው፤ "ይህም መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ያመላክታል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን አካዳሚው ዘርፉን በሚመለከት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በተጨማሪ በምስራቅ አፍሪካ ላሉ ሀገራት የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማከናወን ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።
የደረጃዎች አካዳሚው 16 የመማሪያና ከ40 በላይ የመኝታ ክፍሎችን ያካተተ ነው።
የኢትዮጵ ደረጃዎች ኤጄንሲ 50ኛ ዓመት ምስረታን በማስመልከት ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ኤግዚቢሽን በኤጀንሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ለህዝብ ክፍት ሆኗል፡፡