ቀጥታ፡

"በኢትዮጵያ ጉዳይ የዳር ተመልካች ዜጋ መኖር የለበትም " ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2013" (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ጉዳይ የዳር ተመልካች ዜጋ መኖር የለበትም፤ ሁሉም ያገባኛል ብሎ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ ይገባዋል" ሲሉ በምርጫው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግል የሚወዳደሩት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ።

ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ክልል 28 በተመረጡ ስድስት አካባቢዎች የጎዳና ላይ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂደዋል።

በቅስቀሳው ወቅትም ኢትዮጵያ ከራሳቸው አልፈው ለአገር የሚያስቡ ሰዎች እንደሚያስፈልጓት ተናግረዋል።

"ብዙ አይነት ምግብ በአንድ መሶብ እንደሚቀርብ ሁሉ በሀገሪቱ ያለው የብሔርና የሃይማኖት ብዝሃነት የጠንካራ አንድነት ምንጭ ነው" ብለዋል።

ነገር ግን አሁን ላይ በብሔር፣ ሃይማኖት፣ አስተሳሰብና ፖለቲካ አጥር ሰርተናል ሲሉም ነው የተናገሩት።

ዓላማቸው ብዝሃነትን በማስተናገድ የጥላቻና ልዩነት አጥርን አፍርሰው ድልድይ መገንባት መሆኑን ገልጸው፤ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቴ "ሐ" ነው ምረጡኝ ብለዋል።

ዜጎች የመራጮች ምዝገባ ቀን መራዘሙን እንደ እድል በመጠቀም የምርጫ ካርድ እንዲያወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ጥቂቶች የሚጫወቱበት ብዙሃኑ የሚሳተፉበት ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ አስተዋጽኦ የሚሻ ነው ብለዋል።

በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ይህን ተገንዝቦ የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበት ተናግረዋል።

በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድ አገር ልጆች መሆናቸውን በመረዳት ከመገፋፋት ወጥተው በሀገር ጉዳይ መተባበር ይገባቸዋል ብለዋል።

ፓርቲዎች ማሸነፍ የሚችሉት በቅድሚያ "ኢትዮጵያ ስታሸነፍ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ደግሞ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና መከባበር የሚስተዋልበት መሆን እንዳለበት መሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናግረዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያን የገጠሟትን ችግሮች ማቃለል ብሎም መፍታት የምንችለው ተጋግዘን በመስራት ነው ብለዋል።

ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ክልል 28 ስር በየካ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 9 እስከ 13 እንዲሁም ቦሌ ወረዳ 10  ላይ በግል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግል ይወዳደራሉ።            

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም