ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ለ6ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ መሠረቱ

ድሬዳዋ ግንቦት 1/2013 (ኢዜአ) - በድሬዳዋ አስተዳደር ለ6ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ህጋዊ ዕውቅና አግኝተው የሚወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ መሠረቱ ።

ፓርቲዎቹ የመሰረቱት የጋራ መድረክ በምርጫው ሂደት ለሚፈጠሩ ችግሮች ፈጣን መፍትሄ በመስጠት ምርጫው ነጻና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚያግዝ መሆኑ ተመልክቷል።

በድሬዳዋ ከሚወዳደሩ አስር ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ውስጥ ዘጠኙ ዛሬ በተካሄደው የጋራ መድረክ ምስረታ ላይ በመሳተፍ  መድረኩ በሚመራበት የአሠራር ደንብ ላይ የስምምነት ፊርማቸውን በማኖር አፅድቀዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የድሬደዋ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየስ በስነ -ስርአቱ ላይ እንደገለጹት የጋራ መድረኩ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበት ነው።

"መድረኩ ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ ለሚፈጠሩ ችግሮች የጋራ መፍትሄ በመስጠት ምርጫው ሰላማዊና በህዝብ ዘንድ ታአማኒነትን ያረጋገጠ እንዲሆን ያስችላል "ብለዋል።

"በተፈረመው ደንብ መሠረት ህዝብን ከሚያጋጩ ድርጊቶች በመራቅ ለደንቡ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት መስራት አለብን "ሲሉ ተናግረዋል።

የጋራ መድረኩ መመሥረት በፓርቲዎች መካከል የተሻለ ቅርርብ የሚፈጥርና አንድ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይን በመመካከርና በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር ለመፈፀም እንደሚያግዝ የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተወካይ አቶ ዮናስ በትሩ ናቸው።

የእናት ፓርቲ ተወካይ ወይዘሪት ቃልኪዳን አዳነ በበኩላቸው "መድረኩ በመቀራረብ የተሻለ ተግባር ለመከወን ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል" ብለዋል።


በተለይ እናት ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዕድል የሚፈጥርለት መሆኑን ተናግረው ለተሳካ ውጤት ሁሉም የአሰራር ደንቡን አክብሮ በመስራት ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል ።


የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ተወካይ አቶ ጀማል ዑመር በበኩላቸው "የጋራ መድረክና የአሠራር መመሪያ ዘርግቶ በጋራ መስራት ምርጫው ያለችግር በህዝብ ዘንድ ተቀባይና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያስችላል" ብለዋል።

የጋራ መድረኩ ዜጎች በምርጫው ላይ ተሳትፏቸው እንዲጎለብት የሚያግዝ መሆኑንም አመልክተዋል ።


በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን የጋራ መድረኩ የምስረታ ሂደት ከወር በፊት ተጀምሮ ዛሬ ዕውን መሆኑን ተናግረዋል።

መድረኩ ፓርቲዎች በጋራ በመመካከርና በመረዳዳት ለመስራት እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል ።

እንደ  ኃላፊው ገለጻ መድረኩ የጋራ ምክር ቤትና የተለያዩ ጊዜያዊ ኮሚቴዎች በማዋቀር ስራዎችን የሚያከናውን ሲሆን በቀጣይ ቀናት የመድረኩን አመራሮች በጋራ ይመርጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም