ተፈናቃዮችን በመደገፍ በኩል የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ተፈናቃዮችን በመደገፍ በኩል የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
አሶሳ (ኢዜአ) ግንቦት 1/2013 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ለሚደረገው ጥረት ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የሚሰጡት ምላሽ የሚያበረታታ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
በክልሉ ካማሽ ዞን ሰዳል ወረዳ እና ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ እና ባቦገምቢል ተፈናቅለው በባምባሲ ጊዜያዊ መጠለያ ለሚኙት 3 ሺህ 800 በላይ ተፈናቃዮች ትናንት የእለት ደራሽ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታረቀኝ ተሲሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ የተፈናቀሉትን ወገኖችን መደገፍ እና ማቋቋም ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ ነው።
ይህንኑ መሠረት በማድረግ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን ያስታወሱት አቶ ታረቀኝ የሚበረታታ ምላሽ እየተገኘ መሆኑንም አመልክተዋል።
በባምባሲ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ትናንት በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና አክሽን ፎር ዘ ኒድ የተባለ ድርጅት የቀረበውን ተከታታይ ድጋፎችን አቶ ታረቀኝ በአብነት ጠቅሰዋል።
በደጋፉ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁስ፣ አልባሳት፣ ድንኳኖች እና ሌሎች የሚገኙበት ሲሆን ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት አስረድተዋል።
በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የአሶሳ ማስተባበሪያ ሃላፊ ሚስ ጆላንዳ ቫን ድርጅቱ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጪ ሃገር ስደተኞች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮችም ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በመተከል ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከተለያዩ በጎ አድራ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ድርጅቱ ያደረገውን ድጋፍ አስታውሰዋል።
የዘንድሮው ክረምት ተጠናክሮ ከመግባቱ አስቀድሞ ለመተከል ተፈናቃዮች ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ድርጅቱ እያከናወነ የሚገኘው ጥረት እንዳለ ሚስ ጆላንዳ አመልክተዋል።
የአክሽን ፎር ዘ ኒዲ አሶሳ ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ መላኩ ጉተማ ድርጅቱ ትናንት ያደረገው ድጋፍ ሌሎች በጎ አድራጊ ድርጅቶች ለተፈናቃዮች ትኩረት እንዲሰጡ በማሰብ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ከድጋፉ በተጨማሪ ተፈናቃዮች ራሳቸውን መልሰው የሚያቋቁሙበት ስነልቦና እንዲላበሱ የሚያደርግ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ከመንግስት ጋር የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ድጋፉን ካገኙ ተፈናቃዮች መካከል ወይዘሮ አትጠገብ ጸሐይ እንዳሉት ድጋፉ የቤተሰቦቻውን ዕለታዊ ፍጆታ መሸፈን አስችሏል።
በቀጣይም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
አቶ ጌታቸው ስጦቴ የተባሉ ተፈናቃይ በበኩላቸው በሰዳል ወረዳ በገጠመን ጥቃት ቤተሰቦቻችንን እስከማጣት የደረሰ የከፋ ጉዳት ደርሶብናል ብለዋል።
ይሁን እንጂ የባምባሲ ህዝብ እና መንግስት በየዕለቱ ምግብ እና ሌሎች ድጋፎችን ሲያደርጉላቸው በነበረው ድጋፍ መጽናናታቸውን አስረድተዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት ከክልሉ ከማሺ ዞን ሰዳል ወረዳ እና ከምዕራብ ወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች በባምባሲ ጊዜያዊ መጠለያ ይገኛሉ።