ቀጥታ፡

ኢሳት የህዝብ ሚዲያ ሆኖ ተቋቋመ

ግንቦት 01 / 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ከግል ሚዲያነት ወደ ነጻ የህዝብ ሚዲያነት ተቀይሮ በይፋ ተቋቋመ።

ኢሳት በአዲሱ የሚዲያ አዋጅ ድንጋጌ መሰረት በአገር ውስጥ እስካሁን ከተደራጀበት የግል አክሲዮን ድርጅትነት ወደ ልዩ የህዝብ ሚዲያነት የተቀየረበትን የምስረታ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተከናውኗል።

በዚህም ሚዲያው "በሙሉ ገለልተኛነት ከፖለቲካ፣ ከብሄር፣ ከሃይማኖት እንዲሁም ከሌላ ወገንተኝነት በመራቅ ይሰራል" ተብሏል።

በመሆኑም ኢሳት በትናንትናው እለት 16 የቦርድ አባላት ተመርጠውለታል።

ኢሳት ከሚመራበት የሚዲያ መርሆችና ኤዲቶሪያል ፖሊሲዎች አንስቶ በተቋሙ ባለቤትነትም ሆነ በአደረጃጀት የተሰጠው ቁመና በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ የሚመጥን ነጻና ገለልተኛ ህዝባዊ ሚዲያ ሆኖ ስለመመስረቱ ተገልጿል።

የኢሳት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የህዝብ ሚዲያ ለማደራጀት የሚፈቅድ ህግ አልነበረም።

አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ይህን የሚፈቀድ በመሆኑ ኢሳት በአዲስ መልክ በህዝብ ሚዲያነት በመደራጀት አገልግሎት ለመስጠት የመተዳደሪያ ደንብ አጽድቆ የቦርድ አባላት መመረጣቸውን ገልጸዋል።

በአገሪቷ የመንግስትና የግል ሚዲያዎች ህዝቡን ለመድረስ የሚጠበቅባቸውን ያህል እየተንቀሳቀሱ አለመሆኑን የጠቀሱት አቶ አንዳርጋቸው፤ ኢሳት በዚህ ጉዳይ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ኢሳት በህዝቡ ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ችግር ነቅሶ በማውጣት ለመዘገብና ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

'ኢሳት ነጻ ሚዲያ ማህበር አገር በቀል ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት' በሚል ስያሜ በሚያዚያ 2013 ዓ.ም በይፋ የህዝብ ሚዲያ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም