ቀጥታ፡

ፖሊስ ኢትዮጵያን ሰላም ለመንሳት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን የመመከት ተግባሩን ያጠናክራል- ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ

አዲስ አበባ ግንቦት 1 /2013 (ኢዜአ) ፌዴራል ፖሊስ በውጭም በውስጥም ኢትዮጵያን ሰላም ለመንሳት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን የመመከት ተግባሩን ያጠናክራል ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተናገሩ።

ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል በ19ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 6 ሺህ 431 የፖሊስ አባላት አስመርቋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል 7 መቶ 92 የሚሆኑት የአፋር ክልል ልዩ ኃይል አባላት መሆናቸውም ተገልጿል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፤ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ከፖሊስ አባላቱ ጥረትና ትጋት መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሰላም ለማወክ በውጭም በሀገር ውስጥም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህንን እኩይ አላማ በማክሸፍ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በትኩረት ይሰራሉ ብለዋል።

በየአካባቢው የተሸሸጉ ወንጀሎኞች የንጹሃን ዜጎችን ህይወት እየቀጠፉ፣ ሞትና መፈናቀል እያስከተሉ በመሆኑ አድኖ ለህግ የማቅረብ ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ፌዴራል ፖሊስ የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን የመመከት ተግባሩን ያጠናክራል ብለዋል።

ተመራቂ የፖሊስ አባላትም የሃገርን ህልውና እንዲሁም የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ አክለውም በኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በነጻነት ተዘዋውሮ ህይወቱን እንዲመራ ማስቻል ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የሁሉም ዜጎች መብትና የአገሪቷ ሉአላዊነት እንዲከበር ለማድረግ ከተመራቂዎቹ ከፍተኛ ቁርጠኝነትና ስራ ይጠበቃል ብለዋል።

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ አጠቃላይ ሂደትም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተመራቂ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከሌሎች የጸጥታ አከላት ጋር በጋራ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ፌዴራል ፖሊስ በሚያደርገው ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉም ለተመራቂዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

ተመራቂ የፖሊስ አባላቱም በስልጠናው የጨበጡትን እውቀት በመጠቀም አገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የፖሊስ ስነ ምግባር በሚያዘው መሰረት ያለ አድሎ ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ ከሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የተወጣጡ ሲሆን በቆይታቸውም አጠቃላይ የፖሊስ ሳይንስ ምንነት፣ ስለ ሕገ መንግስት ጉዳዮችና ፖሊሳዊ ስነ ምግባርን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ስለጣናዎችን ወስደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም