ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢጀንሲ ያስገነባው ዘመናዊ የስልጠና ማእከል ተመረቀ

ደሴ ግንቦት 1 /2013 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ ከሁሉም በፊት የሀገሩን ሰላምና አንድነት በማስቀደም ሊንቀሳቀስ እንዳለበት የሐይማት አባቶች አሳሰቡ፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ሐይማኖት ፎረም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትላንት  በደሴ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ክፍል ኃላፊ ሊቀ ሰይማን ስነፀሃይ አድማሴ እንደገለጹት ሰላም ከምንም በላይ ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ ነገሮች ሁሉ እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡

ሰላም ለአፍታም እንኳ ከሌለ ፈጣሪን ማምለክም ሆነ እንደልብ ወጥቶ መግባትና ሰርቶ ሃብት ማፍራት ሊታሰብ የማይችል ከንቱ ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ከሁሉም በላይ ለሰላምና ለአንድነት ሌት ተቀን ከማንኛውም ጉዳይ አስቀድሞ መስራት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

''በተለይም የውጭና የውስጥ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚሰሩበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ በመሆናችን ልዩነቶቻችን ወደ ጎን ትተን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ በጋራ ለሀገራችን የምንቆምበት ወቅት ላይ እንገኛለን'' ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኗም ስለ ሰላምና አንድነት አብዝታ ታስተምራለች ያሉት ሊቀ ሰይማን በሰው ልጅ ቀርቶ በእንሰሳት ላይ እንኳ መፈጸም የሌለበት ግድያና መፈናቀል እንዲቆም ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሌላው የዞኑ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ተወካይ ሸህ ሰይድ ዘይን በበኩላቸው ቁርዓንና ሀዲስ ስለ ሰላምና አንድነት አብዝቶ ያስተምራል ብለዋል፡፡

"ምዕምናኑም ይህንኑ መመሪያ በመተግበር ለሰላምና አንድነት ዘብ በመቆም እምነቱን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡

''ወጣቱም በእምነትና በብሔር ሊከፋፍሉ ለሚፈልጉ የሴራ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ ሳይሆን አባቶቻችን በአንድነት በአጥንትና በደማቸው ዳር ድንበሯን አስጠብቀው ያስረከቡንን ሀገር የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል'' ብለዋል፡፡

''ወቅቱ በጥቃቅን ነገሮች የምንነታረክበት ሳይሆን ሀገራችንን ለመቀራመት ካሰፈሰፉ ጠላቶቻችን ለማዳን በጋራ የምንታደግበት ወቅት አሁን ነው'' ያሉት ደግሞ የሰሜን ምስራቅ ክልል ወንጊላዊት አብያተ ክርስቲያን ህብረት ዋና ጻህፊ ፓስተር ግርማ ከበደ ናቸው፡፡

ሰላምና አንድነት ለመፍጠር ተባብሮ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው "የሁሉም እምነት ሰላምና አንድነትን እንጅ ክፋትና መገዳደልን ያወግዛል" ብለዋል፡፡

በማዕከላዊ ሰሜን ኢትዮጵያ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነየሱስ የወንጌል መምሪያ ኃላፊ ቄስ ሙሉጌታ አለሙ በበኩላቸው ምዕምናኑ ህብረተሰቡን በእምነትና በብሔር ለመከፋፈል የሚሰሩ ፖለቲከኞችን በግሰፅና መቃወም "ይገባል።

አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች የሚሆንበት ዘመን ማለፉን ጠቁመው አባቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራንና መንግስት ለሰላምና አንድነት አብዝቶ መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል።

"ኢትዮጵየን ከጠላቶች ለመጠበቅና የህብረተሰቡን አንድነት ለማስቀጠል የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን" ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኮላቸው "ወሎን የብጥብጥ ቀጠና ለማድረግ የሚሰሩ የጥፋት ኃይሎችን በጋራ መመከት ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

የሐይማት አባቶች በእየእምነት ተቋማቸው ሰላምና አንድነትን በመስበክ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለማስቀጠል የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለየ መልኩ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡም አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲገጥሙት ጥቆማ በመስጠት ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

በደሴ ከተማ በተካሄደው የፎረሙ ውይይት የሐይማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም