በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት የሰራተኞች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ገለጸ

147

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት በተለያዩ መስኮች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሰራተኞች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ገለጸ።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኮንፌዴሬሸኑ በዘንድሮው ምርጫ ለፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ የማመቻቸት እና ለሰራተኞች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ይሰራል።

በምርጫው ሂደት ኮንፌዴሬሸኑ ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ በታዛቢነት የሚከታተል መሆኑንም ገልጸዋል።

"በተለያዩ መስኮች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሰራተኞች በምርጫው ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን መጠቀም አለባቸው" ብለዋል።

ለአገሪቱ፣ ለሰራተኛው ብሎም ለአጠቃላይ ህዝቡ ይጠቅማል የሚሉትን ፓርቲ በመምረጥ አገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የምርጫ ካርድ አለመውሰድ እና አለመምረጥ መብትን ለሌሎች አሳልፎ መስጠት መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሰራተኞች በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ የዜግነት ሃላፊነታቸው እንዲወጡ ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም