የፖሊስ ሀይሉ የሀገርና የህዝብ ሰላምና ደህንነት የማስከበር ሀላፊነቱን በትጋት ሊወጣ ይገባል-አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የፖሊስ ሀይሉ የሀገርና የህዝብ ሰላምና ደህንነት የማስከበር ሀላፊነቱን በትጋት ሊወጣ ይገባል-አቶ አገኘሁ ተሻገር
ደብረማርቆስ፣ ሚያዝያ 30/2013 (ኢዜአ) የፖሊስ ሀይሉ የሀገርና የህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ የሚሯራጡ ሀይሎችን ለመመከት ከመቼውም በላይ ሀላፊነቱን እንዲወጣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስገነዘቡ።
በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ከሶስት እስከ አራት ወራት ያሰለጠናቸውን የልዮ ሐይል ፖሊስና እጩ መኮንኖችን ዛሬ አስመርቋል ።
ርእሰ መስተዳድሩ በስነ ስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የክልሉን ፖሊስ ሃይል በማጠናከር የህዝብን ሰላምና ደህንነት አስተማማኝነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
“የፖሊስ ሀይልን ማጠናከር በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጥቃት መመከት ማለት ነው “ ብለዋል።
የፖሊስ ሀይሉ የሀገርና የህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ የሚሯራጡ ሀይሎችን ለመመከት ከመቼውም በላይ ሀላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዘበዋል።
“ምሩቃን በሰለጠናችሁበት ሙያ በመጠቀም ህዝብና መንግስት የጣለባችሁን ሀላፊነት በመወጣት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር እየገጠመ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመቋቋም ቁርጠኛ መሆን አለባችሁ “ብለዋል።
“በተለይ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ፣ እንዲሁም ሰላምና አንድነት ለማደፍረስ ሌት ከቀን ለሚታትሩ የውጭና የውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎችን ለመመከት ጉልህ ድርሻ የምትወጡበት ጊዜ ስለሆነ ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅባችኋል” ሲሉም ተናግረዋል።
የፖሊስ አባላት የዘንድሮ 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል ።
የኮሌጁ ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አንማው አለሜ በበኩላቸው መንግስት የፖሊስ ኃይልን በማሰልጠን የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል ።
“ተመራቂዎች የህግ የበላይነትን በማስፈን ዜጎች ያለምንም የፀጥታ ችግር ወጥተው እንዲገቡ የሚያስችል በሳይንስ የተደገፈ ስልጠና የወሰዱ ናቸው” ብለዋል።
ከተመራቂዎች መካከል ኮንስታብል አስቴር ንጉሴ” በወስድኩት ስልጠና መሰረት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በትጋት እሰራለሁ” ብለዋል።
"የፖሊስ ሚና ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ ማስቻል በመሆኑ መንግስት የሚሰጠኝን ተልኮ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” ያሉት ደግሞ ኮንስታብል ሙሀባው በለጠ ናቸው።
የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ከተቋቋመ 1985 ዓ.ም ጀምሮ በአድማ ብተናና በልዩ ኃይል ፖሊስ እንዲሁም በእጩ መኮንንነት ከ48ሺህ በላይ ሰልጣኞችን ማስመረቁን በስነ ስርአቱ ላይ ተመልክቷል ።