ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን ምልምል የፖሊስ አባላት አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን ምልምል የፖሊስ አባላት አስመረቀ
ሚያዚያ 30/2013 ( ኢዜአ) ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን ከ6 ሺህ በላይ ምልምል የፖሊስ አባላት አስመረቀ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት በማስተላለፍ የስራ መመሪያም ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥም ከውጭም ያሉ ጠላቶች እየጣሩ መሆኑን አንስተዋል።
የዜጎች ህይወት በመቅጠፍና ንብረቶችን በማውደም ጭምር የተቀናጀ የጥፋት ተልእኳቸውን ለመፈፀም እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠልና የህዝቦቿን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የፖሊስ አባላት የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በዚህ ሂደት ለምርቃት የበቁት ምልምል ፖሊሶች ሀገራዊና ህዝባዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ኮሚሽነር ጀነራሉ አሳስበዋል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲከናወንም የፖሊስ ሃይሉ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በህገ መንግስቱ መሰረት አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልግል ዝግጁ መሆናቸውን ተመራቂዎቹም አረጋግጠዋል።
በጦላይ ወታደራዊ ማስልጠኛ ማዕከል ሰልጥነው በዛሬ እለት ለምርቃት የበቁት 6 ሺህ 431 ምልምል ፖሊሶች ናቸው።
ከእነዚህ መካከል 792ቱ የአፋር ክልል ፖሊስ አባላት መሆናቸውም ታውቋል።