ቀጥታ፡

ፈተናዎች ሳይበግሩን ልማታችንን በማከናወን ኢትዮጵያን ወደ ልማትና ብልፅግና እንወስዳታለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ሚያዚያ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) የገጠሙን ፈተናዎች ሳይበግሩን በአንድ እጃችን ጠላቶቻችንን እየመከትን በሌላ እጃችን እያለማን ኢትዮጵያን ወደ ልማትና ብልፅግና እንወስዳታለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሞጆ -ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ አካል የሆነውን የሞጆ- መቂ- ባቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በዛሬው እለት መርቀዋል።

የሞጆ-ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ 202 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ግንባታው የሚከናወነው በሁለት ምእራፍ ተከፍሎ ነው።

92 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው እና የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነው ከሞጆ- መቂ- ባቱ የፍጥነት መንገድ ግንባታው ተጠናቆ በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጉዞን ለማቅለል፣ ቀልጣፋ የሆነ ግንኙነት ለመፍጠር አውራ ጎዳና ብቻ ሳይሆን ቀልጣፋ እና ለጉዞ ምቹ የሆኑ መንገዶች ያስፈልጋሉ።

ሀገር የሚገነባው አልጋ በአልጋ በሆነ ምቹ ሁኔታ ሳይሆን ፈታኝ ችግሮችን በመጋፈጥ መሆኑንም አስረድተዋል።

"በመሆኑም የገጠሙን ፈተናዎች ሳይበግሩን በአንድ እጃችን ጠላቶቻችንን እየመከትን በሌላ እጃችን እያለማን ኢትዮጵያን ወደ ልማትና ብልፅግና እንወስዳታለን" ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን ጸጋዎች ተጠቅመን ለልጆቿ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገሮች የምትተርፍ ሀገር እንገነባለንም ነው ያሉት።

ብልጽግና እውን የሚሆነው ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ሲገነቡ በመሆኑ አገር ካለ መንገድ ግንባታ እድገትና እንቅስቃሴዋ እንደማይሳካ ተናግረዋል።

ለሰው ልጅ የደም ስር ያለውን ዋጋ ያክል መንገድም ለእድገትና ብልፅግና በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሞጆ -ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለውን የንግድ ትብብርና የልማት ትስስር ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ፣ ከኤርትራና ከሱዳን የሚያገናኛትን መንገዶች በመገንባት ላይ እንደምትገኝም ጠቁመዋል።

በአለም ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር ሊሰራ የታሰበው የአዳማ- አዋሽ የፍጥነት የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በቀጣይ እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ እውን ሲሆን ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ያለውን የሎጅስቲክስ አገልግሎት ሂደት ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብና ኢትዮጵያን ወደ ሚፈለገው የእድገት ከፍታ ለማድረስ የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የትራንስፖርት ዘርፉን ምቹና ተደራሽ ለማድረግ ብሔራዊ የትራንስፖርት ፖሊሲ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሞጆ-መቂ-ባቱ የፍጥነት መንገድ ያሉ የግራና ቀኝ ሰፊ ስፍራዎች ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ታሳቢ በማድረግ መልኩ መዘጋጀቱንም ነው የገለጹት።

መንገዱ የንግድ ልውውጥን ከማሳለጥ ባሻገር የአካባቢውን የተፈጥሮ ምህዳርን ለመጠበቅ አይነተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።

መንገዱን የሚጠቀሙ ሁሉም ባለድርሻ አከላት ለመንገዱ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ፤ መንገዱ ዘመኑ ያፈራቸው ከፍተኛ የፍጥነትና የክብደት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይ አስር ዓመታት አዲስ አበባን ከሌሎች የሀገሪቱ ኮሪደሮች የሚያገናኙ ተጨማሪ የፍጥነት መንገዶች እንደሚገነቡም ገልጸዋል።

የአዋጭነት ጥናት የተጀመረባቸው እንዳሉም ነው የጠቆሙት።

የሞጆ ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ከካይሮ እስከ ኬፕታውን የሚዘረጋው የትራንስ አፍሪካ ሃይዌይ ፕሮጀክት አካል ሲሆን ቀጠናዊ ትብብርና የንግድ ልውውጥን ለማሳለጥ የሚያግዝ ነው።

የትራንስ አፍሪካ ሃይዌይ ፕሮጀክት ዘጠኝ የተለያዩ የግንባታ ኮሪደሮች ያሉት ሲሆን 52 ሺህ 450 ኪ. ሜትር ርዝመት እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም