የማዕድን ዘርፍ ግብይትን ለማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድን ዘርፍ ግብይትን ለማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እና ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድን ዘርፍ ግብይትን ለማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ዑማ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ ተፈራርመዋል።
አቶ ወንድማገኝ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ ዘመናዊ የገበያ ማዕከልና አሰራርን ለመዘርጋት ያስችላል።
ግልጽነት የተሞላበት አሰራር ለማስፈንም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም በማሳደግ ሕገ ወጥ የማዕድን ንግድን ለመቀነስ እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡
"ግብይቱ ዘመናዊነት ተላብሶ እንዲካሄድ ያስችላል" ብለዋል።
በዲጂታል ቴክኖሎጂ ግብይትና መረጃ ለመሰብሰብና ዓለም አቀፍ የማዕድን ዋጋን በየዕለቱ ለማግኘት እንደሚረዳም ገልጸዋል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው "ስምምነቱ ማዕድን አምራቾች በዓለም ገበያ ዋጋ መሰረት በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል" ብለዋል።
በተጨማሪም የማዕድን ምርት ሰንሰለቱን በማሻሻልና በባህላዊ መንገድ የሚደረገውን ግብይት ወደ ዘመናዊነት ለመቀየር እንደሚጠቅም ተናግረዋል።