የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃን ቀን የምናከብረው በጎ ፈቃደኞች በፅናት ለሰብዓዊነት ያሳዩትን ቁርጠኝነት በማስታወስ ነው -ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃን ቀን የምናከብረው በጎ ፈቃደኞች በፅናት ለሰብዓዊነት ያሳዩትን ቁርጠኝነት በማስታወስ ነው -ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
ሚያዚያ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) የዘንድሮውን የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃን ቀን የምናከብረው በጎ ፈቃደኞች በፅናት ለሰብዓዊነት ያሳዩትን ቁርጠኝነት ለማስታወስና የሰብዓዊነት አርማቸውን በማንገብ ለማስቀጠል መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የበላይ ጠባቂ ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በነገው እለት የሚከበረውን የዓለም የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ቀን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዘንድሮው የቀይ መስቀል ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ''የማይገቱ (#Unstoppable)'' በሚል መሪ ሃሳብ በነገው እለት ለ74ኛጊዜ ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ''ፅናት’’ በሚል መሪ ሃሳብ ለ63ኛ ጊዜ ይከበራል።
መሪ ቃሉ የተመረጠው በመላው ዓለም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ ሰዎችን የሚታደጉ በጎ ፈቃደኞች፤ ሠራተኞች፣ የሕክምና ባለሙያዎች በችግሮች መጠንና ስፋት ሳይበገሩ ሰብዓዊ ተግባራቸውን እንደሚወጡ ለማሳየት ነው ብለዋል።
የሚያጋጥሟቸው የርዕዮተ አለም፣ የዕምነት፣ የፖለቲካ፣ የዘርና የፆታ ልዩነቶች ሳይበግሯቸው ያለ አድልዎ፣ በገለልተኝነትና የአሰራር ነፃነታቸው ተጠብቆ፣ የተረጂዎችን ህይወት ለመታደግ ኑሯቸውንም መልሶ ለማቋቋም ቅድሚያ የሚሰጡት ለሰብዓዊነት ባላቸው ‘ፅናት’ መሆኑንም እንዲሁ።
በኢትዮጵያ ዕለቱን የምናከብረው፣ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች የማኅበሩን በጎ ፈቃደኞች፣አባላት፣ የህይወት መስዋዕትነትን ጨምሮ ለከፈሉት ዋጋ፣ በፅናት ለሰብዓዊነት ያሳዩትን ቁርጠኝነት ለማስታወስና የሰብዓዊነት አርማቸውን አንግበን ዓላማቸውን ለማስቀጠል ነው ብለዋል፡፡
እለቱን የምናከብረው በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ውድ ሕይወታቸውን ባጡበትና በተፈናቀሉበት ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ማህበሩ በግንባር ቀደምትነት ወገኖቻችንን ለመታደግ ያደረገው ከፍተኛ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው የችግሩ ስፋት ከሚገመተው በላይ ነው ብለዋል።
''ሕዝባችን ላይ የሚደርሰውን መከራ ቢያንስ መቀነስ ፣ ቢቻል ማቃለል የቀይ መስቀል ማህበር ተልእኮ ቢሆንም እንደዚህ መሰል ችግር ውስጥ እንዳይገባ አስቀድሞ መከላከልን ባህል ማድረግ ይጠበቅብናል'' ብለዋል ፕሬዝዳንቷ በመልእክታቸው።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በሰብዓዊ ሥራዎች የመንግስት አጋዥ በመሆን ለ86 ዓመታት የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ የሰብዓዊነት መርሆዎችን መሠረት በማድረግ ችግሮች በሚከሰቱባቸው ስፍራዎች ሁሉ ቀድሞ በመገኘት የሚያከናውናቸው ሰብዓዊ ተግባራት መበረታታትና መደገፍም አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት፣ አጋር ድርጅቶች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ በመላውዓለም የሚኖሩና ሰብዓዊነትን የሚደግፉ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የኢትዮጵቀይ መስቀል ማህበር እያበረከተ ላለው ሰብዓዊ ተግባር ላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።