“ህወሓት” እና “ሸኔ” ሽብርተኛ ተብለው መፈረጃቸው ዜጎች በማህበራዊ ሕይወታቸው በሠላም እንዲቀሳቀሱ ያስችላል..የሕግ ምሁሯን - ኢዜአ አማርኛ
“ህወሓት” እና “ሸኔ” ሽብርተኛ ተብለው መፈረጃቸው ዜጎች በማህበራዊ ሕይወታቸው በሠላም እንዲቀሳቀሱ ያስችላል..የሕግ ምሁሯን
ሐዋሳ ሚያዚያ 29/2013 (ኢዜአ)“ህወሓት” እና “ሸኔ” የተባሉ ፅንፈኛ ቡድኖች ሽብርተኛ ተብለው መፈረጃቸው ዜጎች በማህብራዊ ሕይወታቸው በሠላም እንዲቀሳቀሱ ከማስቻል ባለፈ የጥፋት ቡድኖቹ በህግ ፊት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር የህግ ምሁሯን አስታወቀ።
የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከላካይ ጠበቃ ቢንያም ከበደ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከህግ አግባብ አንድ ቡድንን በሽብርተኝነት ሊያስፈርጁ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች አሉ።
"ከድንጋጌዎች መካከል ሰዎችን በማህበራዊ ህይወታቸው በሠላም እንዳይንሳቀሱና ንብረት ማፍራት እንዳይችሉ ማድረግ ፣በመሠረታዊ ልማቶች ላይ አደጋ ከማድረስ ባለፈ የሰውን ህይወትና ንብረት ማጥፉትና ማፈናቀል በሽበርተኝነት ያስፈርጃል" ብለዋል።
ከዚህ አንፃር “ህወሓት” እና “ሸኔ” የተባሉ ቡድኖች ለሀገርና ለማህበረሰቡ ስጋት፣ፍርሃትና ሽብርን የሚፈጥሩ ሆነው በመገኘታቸው የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ መሠረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን አስረድተዋል፡፡
ውሳኔው ህብረተሰቡ በሠላም ወጥቶ መግባት እንዲችል ያስችላል፣ ሀገሪቷ በተረጋጋ መንፈስ የልማት ውጥኖቿን ከዳር ለማድረስ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር አሸባሪ አካላትን በህግ በመጠየቅ ተገቢውን ቅጣት እንዲቀበሉ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይ ማንኛውም በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ ጥፋቱ ከባድ ስለሆነ ከ10 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እሥራትና ሞት የሚያስቀጣ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የሽብር ወንጀል ተግባራትን አሟልተው የተገኙ ድርጅቶችን በሀገር ደረጃ ሽብርተኞች ናችሁ ብሎ መፈረጁ ለህብረተሰቡ የሚያስገኘው ፋይዳ ብዙ መሆኑን የተናገሩት ተከላካይ ጠበቃው በተለይ ሌሎች ተመሳሳይ የጥፋት ተግባራት ለመፈጸም የተዘጋጁ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማድረግ የማህበረሰቡን ሠላምና ደህንነት ለማረገገጥ እንደሚረዳ አብራርተዋል።
የሽብርተኝነት ወንጀል በባህሪው እንደ ሌሎች ወንጀሎች ተራና ቀላል ሣይሆን በተደራጀና በታጠቀ ኃይል የሚፈጸምና የሚያስከትለውም አደጋ ከባድና ሁሉንም ማህበረሰብ የሚነካ ስለሆነ ሁሉም ዜጋ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ህብረተሰቡ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ሲመካከሩና ሲዘጋጁ ሲመለከት በዝምታ ከማለፍ በመቆጠብ በኃላፊነት ስሜት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት መተባበር እንዳለበት ተናግረዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ረዳት ዳኛ መላኩ ከበደ በበኩላቸው የሽብር ወንጀል በሰው ልጆችና ንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚፈጥርና እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ ዓለም ቀውስ እያስከተለ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በተለይ ወንጀሉ ውስብስብ በሆነ መንገድ የሚፈጸም ስለሆነ ለተጎጂውም ሆነ ለመንግሥት አስቀድሞ ለመቆጣጠር እንደሚያስቸግር ጠቅሰዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለቱን አካላት ምንም እንኳን ህጋዊ ሰውነት ባይኖራቸውም ሽብርተኛ ብሎ መፈረጁ በዚህ ድርጊት የታሳፊ የሆኑ አካላትና ደጋፊዎችን በህጉ መሠረት ለመቅጣት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ውሳኔው በቡድኖቹ ስም የሚንቀሳቀሱና የዘንድሮውን ምርጫ ሰላማዊ ሂደት ለማደናቀፍና ለማወክ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመግታት ሰፊ እድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
"ውሳኔውመንግስት ቡድኖቹን አንጥሮ በማውጣት የህዝብን በሰላም የመኖር መብት እንዲያረጋግጥና የሃገር ህልውናን እንዲያስቀጥል ለማድረግ ይበጀዋል" ብለዋል።