ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ 29/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ ለዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ተጠሪ ሚስተር ኦስማን ዲዮን ተፈራርመዋል፡፡
የዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በዲጂታል ኢኮኖሚ ትግበራ ለማሳካት አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል።
በዚህም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በቴሌኮሙኒኬሽን መስክ ሥራ በመፍጠርና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ስትራቴጂውን እውን እንደሚደረግ ተመልክቷል፡፡
ለአምስት ዓመታት የሚካሄደው ፕሮጀክት ዋነኛ ዓላማዎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ አካታችነት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዋጋ ተመጣጣኝነትና የዲጂታል ሥራ ፈጠራ ናቸው ተብሏል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፤ ለዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከዓለም ባንክ ጋር የተደረገው የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የአገሪቱ የዲጂታል ዘርፍ የተደራሽነት፣ የዋጋ ተመጣጣኝነትና የብሮድባንድ ግንኙነት ጥራት ችግሮች ለማቃለል እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታል እንዲሆንና የግሉ ዘርፍ በመስኩ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ መንግሥት በዘርፉ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ተግባራት የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግና የዲጂታል ኦኮኖሚ አተገባበርን በማጠናከር፣ የመንግሥትንና የግል ዘርፉን ዲጂታል ግንኙነት በማስተሳሰር ስተዋፅኦ እንዳለው ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የዲጂታል ሥራ ፈጠራዎችንና ንግድ ሥራዎችን እንደሚያጎለብትም ተናግረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት መጨረሻ የፀደቀው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂው ለዲጂታል ፋውንዴሽን ነገሮች መካተታቸውን ተናግረዋል።
የ10 ዓመቱን የልማት እቅድ ለማሳካት የብዙ አካላት ተሳትፎና ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱን ወደ ተግባር ለመውሰድ የፕሮጀክት ትግበራ ማዕከል እየተቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚስተር ዲዮን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳና በኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ያለውን ውጤት ዘላቂ በማድረግ የሚያደርጉ ችግሮችን ለመፍታት ፕሮጀክቱ መቀረጹን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በዲጂታላይዜሽንና ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታትና ዘርፉን ለማዘመንና ወደ አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ያስችላል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ አገሪቱ ተመጣጣኝ ዋጋና ከፍተኛ ጥራት ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ለመንግሥት፣ ለንግድ አከላትና ለዜጎቿ ለማቅረብ እንደሚረዳም ገልጸዋል።