ቀጥታ፡

ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ከላከው 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል- ኤጀንሲው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29/2013 ( ኢዜአ) ከዳያስፖራው ባለፉት ስምንት ወራት ወደ ኢትዮጵያ ከተላከው 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ (ሬሚታንስ) መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 39 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት፤ በ2013 በጀት ዓመት ከሬሚታንስ አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን አስታውሰዋል።

በእቅዱ መሰረትም በበጀት ዓመቱ 8 ወራት ዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መላኩን ገልጸዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሬሚታንስ አፈጻጸሙ ላይ የጎላ ተፅእኖ አለማድረሱን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ ዳያስፖራው ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ ተከትሎ ወደ አገር ቤት መላኩን መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

በሕጋዊ መንገድ ብቻ ገንዘቡን ዳያስፖራው ወደ አገሩ ቢልክ ራሱንና አገሩን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላልም ነው ያሉት።

በተያያዘም ባለፉት ስምንት ወራት 4 ሺህ 822 ዳያስፖራዎች የባንክ ሂሳብ ቁጥሮችን በመክፈት ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራትም 39 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስ፣ በቱሪዝምና በአገልግሎት መስኮች ዳያስፖራዎቹ መሰማራታቸውንም ተናግረዋል።

አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ዳያስፖራዎቹ እስካሁን ወደ ስራ የገቡባቸው አካባቢዎች ናቸው።

ባለፈው በጀት ዓመት ከዳያስፖራው 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት መላኩንና 33 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ሥራ መግባታቸውን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ገንዘቡ የተላከው ከሰሜን አሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛ ምስራቅ፣ ከእስያና ከአፍሪካ አገሮች ሲሆን በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚልኩት የገንዘብ መጠን እየጨመረ መጥቷል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም