ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የጥንካሬ ምንጭ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የጥንካሬ ምንጭ  በመንግስቱ ዘውዴ

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ እንደሀገር እንድትቆም ጀግኖች ልጆቿ መስዋዕት የከፈሉላት፣ በየዘመናቱም በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ እያለፈች እዚህ የደረሰች ሀገር ናት። በእነዚህ ውጣ ውረዶች ውስጥ የያኔው ትውልድ ከፍተኛ የህይወት መስዋእትነት ከፍለው ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች ነፃ ሀገር ለአሁኑ ትውልድ አስረክበዋል።

ኢትዮጵያውያን በእነዚህ ዘመናት ውስጥ የጋራ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በሀገር ክብር ሳይደራደሩ ለነፃነታቸው ተጋድሎ አድርገዋል። በህብር ተሰልፈው ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ ኃይል አስጥለዋል። ህዝቡ ዘመናዊ ጦር እስካፍንጫው ታጥቆ ሀገር ለመውረር የመጣውን የፋሽስት ኢጣሊያን ጦር በጋራ የመከተውና ድል ያደረገው በአንድ የንጉሱ ጥሪ ብቻ ነበር። ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያውያንን የመደማመጥና የመከባበር እሴት አጉልቶ ያሳየና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር የሚነገርለት እውነታ ነው።

ኢትዮጵያውያን የሀይማኖት፣ የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህል ወዘተ ልዩነቶች ቢኖራቸውም መታወቂያቸው እርስ በርስ በመገፋፋት ሳይሆን ተደጋግፈውና ተሳስበው በመኖር ነው። ህዝቡ የሀይማኖትም ይሁን የማንነት ልዩነቶች ሳይገድቡት በጋብቻ ተዛምዶ ቤተሰብ ሆኗል፤ በባህል ተሳስሯል ብቻም ሳይሆን ሊነጣጠል በማይችል ደረጃ ተዋህዷል ለማለት ያስደፍራል።

ይህን ለዘመናት የዘለቀው የኢትዮጵያውያን መልካም እሴት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልዩ የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው አካላት እየተሸረሸረ የመጣ ይመስላል። ለዓመታት በተዘራው ዘር ተኮር ፖለቲካ ምክንያት ባልተለመደ መልኩ ዜጎች ከሚኖሩበት ቀያቸው ይፈናቀላሉ፣ ንብረታቸው ይወድማል፣ ግድያና ዝርፊያ ይደርስባቸዋል። የዚህ ዓይነቱ ዜና እለት ተእለት መስማት የተለመደ ሆኗል። ዜጎች በየትኛውም አካባቢ በነፃነት የመኖር፣ ሀብት የማፍራት እና ሰርቶ የመለወጥ ህልማቸው በስጋት የታጀበ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተስተዋሉ የሚገኙት ግጭቶችና በንጹሀን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አብሮ የኖረውን ህዝብ በጥላቻ እንዲተያይ እያደረጉት ይገኛል። ይህ የጥላቻ አተያይ የህዝቦችን የአብሮነት እሴት እንዲሸረሸር ከማድረግ አልፎ የአገሪቱን ሰላምና ህልውና ወደ መፈታተን ደርሷል። በዚህ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ከበስተጀርባ ሆነው የሚሰሩት ሴራም ቀላል የማይባል ነው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሁለት ወሳኝ ጉዳዮችን ለማሳካት በትኩረት እየሰራች ትገኛለች። የመጀመሪያውና ዋነኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መዋጮ እየተገነባ ያለው የህዳሴው ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ማከናወን ናቸው። እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት የሚሹ ከመሆናቸውም በላይ በትግራይ ክልል ከተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ጋር ተዳምሮ ሁኔታው ምእራባውያን እና የታችኞቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገራት ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ እንዲተክሉ አድርጓቸዋል። 

የዘንድሮው ምርጫ በሀገሪቱ ሪፎርም ከተደረገ ከሶስት ዓመታት ወዲህ የሚደረግ የመጀመሪያ ምርጫ ሲሆን ከወትሮው በተለይ መልኩ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት ይጥላል ተብሎ ተገምቷል። ብዙዎች እንደሚገልጹት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም በእውነተኛ የህዝብ ድምጽና ይሁንታ  መሪዎችን የመምረጥ ልምዱ ብዙ የሚነገርለት አይደለም። በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ አካላት ከምርጫ ውጪ ሌሎች አማራጮችን ሲሞክሩ ነበር። ከሶስት ዓመት በፊት በሀገሪቱ ሪፎርም እንዲካሄድ ካስገደዱ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ አስፈላጊነት እንደነበር የሚታወስ ነው። ስለሆነም የዘንድሮ ምርጫ ከተለመደው አካሄድ በተለየ መልኩ እንዲካሄድና በህዝቡ ዘንድ አመኔታ ያለው እንደሚሆን ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ይህ አዲስ መንገድ የሚቀናቀኑ የውስጥም ይሁን የውጭ ኃይሎች ምርጫው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለዘንድሮ እንዲሻገር ሲደረግ የተቃውሞ ድምጾችን አሰምተው እንደነበር ይታወሳል። አሁን ደግሞ የምርጫው ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ በተቻላቸው መጠን ምርጫው እንዳይሳካ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ማድረግ ጀምረዋል። በምርጫው ሰበብ የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ የውስጥም ይሁን የውጭ ሃይሎች አንዳንዶቹ ከወዲሁ በሚያወጧቸው መግለጫዎች ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዳይጠናቀቅ እንደሚሰሩ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የምርጫውን ዝግጅት አስመልክቶ ከክልል ፕሬዝዳንቶች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ስለሁኔታው ሲገልጹ “እነዚህ ኃይሎች በተቻለ መጠን ምርጫው እንዳይሳካ በማድረግ፤ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እንዳይስማሙ በማድረግ ጉዳዩ በድርድር እንዲፈታና የሽግግር መንግስት በማቋቋም እንደአንዳንድ ጎረቤት ሀገራት ደካማ መንግስት ብቻ ሳይሆን የምናዘውን የሚፈጽም መንግስት እንዲመሰረት እናደርጋለን ብለው ዶክመንት አዘጋጅተው ማሰራጨት ከጀመሩ ውሎ አድሯል” በማለት ነበር ያብራሩት።

ኢትዮጵያ የያዘችው ሁለተኛው የትኩረት አጀንዳ የህዳሴው ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሲሆን በመጪው የክረምት ወራት 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለማጠራቀም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ይታወሳል። ግብጽ ለዘመናት “የዐባይ ወንዝ ለግብጽ ከፈጣሪ የተሰጠ ስጦታ ነው” በሚል ኢትዮጵያ በወንዙ እንዳትጠቀም በተለያዩ መንገዶች ጫና አሳድራ ቆይታለች። ይህ ሁኔታ በታሪክ ሂደት ተቀይሮ ኢትዮጵያውያን በቁጭት በመነሳሳት ከየኪሳቸው ባዋጡት መዋጮ የህዳሴው ግድብ ተገንብቶ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን በጣት የሚቆጠሩ ወራት ብቻ ቀርተዋል።                 

ምዕራባዊያኑ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ እየተካሄደ ባለው ድርድር እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተካሄደውን ህግ የማስከበር እርምጃ መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሰሩ ይገኛል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ አምስት ጊዜ ያህል ስብሰባ አካሂዷል። በየስብሰባዎቹ ኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ ለመጣል የተደረጉ ክርክሮች ሩሲያና ቻይና ባለመስማማታቸው ምክንያት ሳይሳኩ የቀሩ ሲሆን በስድስተኛው ስብሰባ የወጣው መግለጫ በተወሰነ ደረጃ መንግስት ለሚያደርገው ጥረት እውቅና የሰጠ ነበር።  ይህ መግለጫ አንዳንድ አካላትን ያስደሰተ አይመስልም። አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ያሳስበኛል በሚል ቀጠናውን በተመለከተ መፍትሔ እንዲያመጡ አንድ ዲፕሎማት የመደበችው ወዲያው ነበር፡፡ የአውሮፓ ህብረትም ተደጋጋሚ መግለጫዎችን እያወጣ ይገኛል።

ብዙዎች እንደሚገምቱት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ይህን ያህል ትኩረት ያደረገችበት ዋና ምክንያት ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታን ማእከል በማድረግ ግብጽ በመካከለኛው ምስራቅ ካላት ተጽእኖ ፈጣሪነት አኳያ በህዳሴው ግድብ የግብጽን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሆን በዚህም የግብጽ ይሁንታ ሳይኖር የሁለተኛው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ ጫና ለመፍጠር ነው። በሌላ በኩል የግድቡ የውሃ ሙሌት በስኬት ከተከናወነ ኢትዮጵያ በቀጠናው የሚኖራትን ተፅዕኖ ከፍ ስለሚያደርገውና በአንፃሩ የግብጽ ተደማጭነት ስለሚቀንስ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታዋ ስለሚጎዳው መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡

የታችኞቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብጽ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የሚከናወን ከሆነ ማናቸውም አማራጮች (ወታደራዊውን ጨምሮ) እንደምትጠቀም በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሁለቱ ሀገራት ግንባር ፈጥረው በኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮች እንዲፈጠሩና እንዲባባሱ በማድረግ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ከፍተኛ ትግል እያደረጉ ይገኛሉ። ሁለቱ ሀገራት የቅኝ ግዛት ውሎችን መነሻ በማድረግ ድርሻችን እንዳይነካብን በሚል ማቀንቀናቸውን አሁንም አጠናክረው ቀጥለዋል።

በቅርቡ ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው ምሁራን እንደገለጹት ግብጽ እና ሱዳን በውስጥና በውጭ የሚሰሩትን መሰናክሎች በማለፍ ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት እውን ለማድረግ መዘጋጀቷ ያልጠበቁት ስለሆነ አሁን የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ ስራ አመራር አካዳሚ የኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ እንደሚሉት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል ሁለቱ አገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዳይኖር እየሰሩ ነው። የግድቡ ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ በበኩላቸው ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር አቅደውና ተዘጋጅተው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። ሀገራቱ በኢትዮጵያ ያለው ብሄር ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው የምሁራኑ እምነት ነው።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ የመልማት መብቷን እንዳታረጋግጥ ከውስጥና ከውጭ ተፃራሪ ሀይሎች በርካታ ጫናዎች እያሳደሩ በመሆኑ በጋራ መቆም የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን። እያንዳንዱ ዜጋ በአሁኑ ወቅት ያሉትን የፖለቲካ ፍላጎቶች በአግባቡ ተረድቶ የውስጥ ልዩነቶችን በማጥበብና በንግግር በመፍታት ለአገር ሉዓላዊነት እና ለህዝቦች ደህንነት በጋራ መቆም ይገባል። ህዝቡ የብጥብጥ ሴራ የሚያሴሩ ሀይሎች በቀደዱት ቦይ ከመፍሰስ ይልቅ የውስጥ አንድነቱን በማጠናከር ጫናዎችን ተቋቁሞ ማለፍ የሚያስችል አቅም መፍጠር ይጠበቅበታል። ምክንያቱም የሀገር ሰላም የሚረጋገጠው እያንዳንዱ ግለሰብ ለሰላም በሚያበረክተው አበርክቶት ላይ የሚመረኮዝ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ለሀገር ሰላም መስፈን የዜጎች ትንሹ ሀላፊነት ነው፡፡

የሀገር ሰላም እና ደህንነት መንግስት በሚያከናውነው ጥረት ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም።  የህዝቦች አብሮ የመኖር እሴቶችን የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት የእያንዳንዱ ዜጋም ጭምር ነው። አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚንቀሳቀሱ እና አንድነቷን ለማጠናከር በሚታገሉ ሀይሎች መካከል ፍልሚያ የሚካሄድበት በመሆኑ በዚህ ወሳኝ ወቅት ፖለቲከኞች በልዩነቶች ሳይሆን በጋራ አስተሳሰቦች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ሁሉም ቤተእምነቶችም ምእመኖቻቸውን በማስተማር ጭምር ነባር እሴቶቻችን እንዲጠበቁ፤ ለሀገር ሰላምና ደህንነት የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል።

የኢትዮጵያ የጥንካሬ ምንጭ የማንም ሳይሆን የኩሩ ህዝቦቿ ነው፡፡ ለዚህም በድህነት ውስጥ መረዳዳትን፣ በልዩነት ውስጥ መቀራረብን፣ በችግር ውስጥ መተሳሰብን በአጠቃላይ አንድነትን እሴቱ ያደረገ ህዝብ ነው። ሀገሪቱ የተደቀነባትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን ተጋፍጣ ማለፍ የምትችለውም ከምንም በላይ ውስጣዊ አንድነቷን በማጠናከር ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም