ምክትል ከንቲባዋ በየካ ክፍለ ከተማ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው 117 ዜጎች መኖሪያ ቤቶችን አስተላለፉ

67

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በየካ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 117 ዜጎች የቀበሌ መኖሪያ ቤቶችን አስተላለፉ።

ለወጣቶችና ሴቶች ሥራ ዕድል ለመፍጠርም 26 የንግድ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።

በክፍለ ከተማው ለ117 ዜጎች የተላለፉት መኖሪያ ቤቶች 468 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው።

የንግድ ቤቶቹ ደግሞ 130 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በከተማዋ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማምጣት አስተዳደሩ ያለመታከት ይሰራል ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የህግ የበላይነትን በማስፍን ሕገ ወጥ አሰራሮችን የማስወገድ ስራውን በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በፕሮግራሙ ላይ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለአትሌት ዋሚ ቢራቱና አትሌት ጌጤ ዋሚ እንዲሁም አርቲስት ችሮታው ከልካይና አርቲስት ሙሉ ገበየሁ የእውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቷል፡፡

በክፍለ ከተማው ሰራተኞች፣ ባለሀብቶችና ትጉህ ማህበራት የዕውቅና እና የገንዘብ ሽልማትም ተበርክቷል፡፡

በቀጣዩ ሳምንት የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር በዓል በማስመልክትም ለ120 የእስልምና እምነት ተከታዮች የበግና ሌሎች የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ በምክትል ከንቲባዋ ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም