ቀጥታ፡

የከተሞችን ዕድገት ለማስቀጠል የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጎለብት ይገባል

ሚያዝያ 28/2013(ኢዜአ) የከተሞችን ዕድገት ለማስቀጠል የግሉ ዘርፍ አጋርነትና ተሳትፎ ሊጎለብት እንደሚገባ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ።

"የከተሞች ሚና ለንግድ መስፋፋት፣ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ" በሚል በመሪ ኃሳብ የከንቲባዎችና የግሉ ዘርፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የከተሞችን ዕድገት ለማስቀጠል የግሉ ዘርፍ አጋርነት ያስፈልጋል።

ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና ሠላማዊ በማድረግ እድገታቸውን ለማስቀጠል የሚያስችል ምቹ ከባቢ ለመፍጠር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጎለብት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጎን ለጎንም ከንቲባዎች እውቀትንና ተሞክሮን መሰረት ያደረገ ወቅቱን የዋጀ የከተማ አመራር ሥርዓት በመዘርጋት ሊመሩ ይገባልም ነው ያሉት።

መንግሥት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝና የግሉ ዘርፍ ተባባሪ እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ስኬት የከተሞች አስተዳዳሪዎችና የነዋሪ ተወካዮች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ አዘዘው በበኩላቸው ከተሞች የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በከተሞች ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት አማራጮችን በቀላሉ ለይተው ለመሰማራት የሚያስችላቸው ፈጣን አሰራር እንዲዘረጋ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጉባኤው ከዚህ አንጻር ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች የዘርፉ ዋነኛ ማነቆዎችን በመለየት የመፍትሄ ሃሳብ ለማስቀመጥ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ጉባኤው አዳዲስ የሥራ ዕድል ሀሳቦችን በማፍለቅ ከተሞች በራሳቸው ገቢ እንዲተዳደሩ፣ ገቢያቸውን ለማሳደግና የነዋሪዎችን ፍላጎት ለማሟላት ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚሁ ጉባኤ የተለያዩ ከንቲባዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም