የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከዲፒ ወርልድ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ - ኢዜአ አማርኛ
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከዲፒ ወርልድ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ
ሚያዝያ 28/2013(ኢዜአ) የትራንስፖርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የበርበራ ወደብ ኮሪደርን ለማልማት ከዲፒ ወርልድ ጋር ስምምነት ተፈራረመ።
ተቋሙ ከሁለት ወራት በፊት የኢንቨስትመንት ጉባኤ አካሄዶ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በጥምረት ሊያለሟቸው የሚችሏቸውን 44 ፕሮጀክቶች ለይቶ እንደነበር ተገልጿል።
በመሆኑም ዲፒ ወርልድ በአለምአቀፍ ደረጃ በወደብ ልማት ዘርፍ ልምድ ያካበተ በመሆኑ ዛሬ በኢትዮጵያ ግዛት የበርበራን ወደብ ለማልማት አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኢንቨስትመንት ለማድረግ ተፈራርሟል።
መንገዶችንና ደረቅ ወደቦችን ለማልማት፤ ትልልቅ መጋዝኖችን ለመገንባት፤ ቀዝቃዛ ፍራፍሬዎችን ፤ አትክልቶችን ለማከማቸትና ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል መጋዝኖችን ለመገንባት ነው ስምምነቱ የተፈጸመው።
ስምምነቱ መሰረተ ልማቶችን መገንባት ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ መስራትን ጭምር ያካተተ ነው።
በቀጣይም ሌሎች ወደቦችን ለማልማት ዕቅድ መያዙን ነው የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የገለጹት።
የጅቡቲ ወደብ አሁንም ዋነኛ የኢትዮጵያ ወደብ ሆኖ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ እርሱ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ባጠረ ጊዜ፣ በዝቅተኛ ወጪ፣ ውስብስብነቱ በቀነሰ መንገድ ገቢና ወጪ ምርቶችን ከአገር ውስጥም ወደ አገር ውጪም ለማስገባት አማራጮችን ማስፋት እንደሚገባ ገልጸዋል።
''በቀጣይ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር እየተፈራረምን አገራችን አሁን ካለችበት የሎጅስቲክ ቅልጥፍና ዝቅተኛ ደረጃ ወጥታ ተወዳዳሪና ከአፍሪካ የምትጠቀስ ሆና መውጣት እንድትችል እንደዚህ አይነት አማራጮችን እንወስዳለን'' ብለዋል።
የትራንስፖርት ዘርፉ እቅድ በቀጣይ 10 አመታት ከሶስት ትሪሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል፤ይህን መሰል ስምምነት ደግሞ በአገር ውስጥ ያሉ ዘርፎችን በማነቃቃት የአሰራር ስርዓቱን በማዘመንና ውድድር በመፍጠር የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
ከደረቅ ወደብ ማልማት ጋር ተያይዞ ከአሁን በፊት ደረቅ ወደብ ማልማት በመንግሰት ብቻ የሚሰራ የነበረ ሲሆን የህግ ማዕቀፉ ተስተካክሎ የውጭ ባለሃብቶች ገብተው ማልማት እንዲችሉ መወሰኑ ይታወሳል።