ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ልምድን በማዳበር ለትምህርት ጥራት መስራት አለባቸው...ሚኒስቴሩ

ደብረ ብርሃን፣ ሚያዚያ 28/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች በውጭ ከሚገኙ አቻቸው ጋር ትስስር ፈጥረው ልምድን በማዳበር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አመለከተ።

ሶስተኛው  አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው፡፡  

በፎረሙ መድረክ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል እንዳሉት፤ መንግስት ለከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

አሁን ላይ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ብቻ ከ46 በላይ በማድረስ  የሰለጠነ የሰው  ሃይል በስፋት በማምረት ኢኮኖሚውን የመደገፍ ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም የትምህርት ጥራትን አስጠብቆ  ብቁ፣ ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጋ በማፍራት  በኩል ክፍተቶች በማጋጠማቸው በዘርፉ ላይ አሉታ ተጽእኖ አሳድሯል ብለዋል።

ችግሩን ለማቃለል ዩኒቨርሲቲዎች ነጻና ገለልተኛ ሆነው የመማር ማስተማር፣ የምርምና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በአዲስ መልክ የማደራጀት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

የወቅቱ ችግር የሆነውን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ  በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውጭ  ከሚገኙ አቻዎቻቸው ጋር ትስስር ፈጥረው ልምድና ተሞክሮ በማዳበር  ለለውጥ መስራት አለባቸው ሲሉ አመልክተዋል።

የፎረሙ ዓላማም በሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን አጠናክረው የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ በማካሄድ በሃገራዊ ግንባታው የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ  ለማስቻል እንደሆነ ተነግሯል።

የደበረ ብርሀን ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ ደረጀ አጄቤ በበኩላቸው  ዩኒቨርስቲው የማህበረሰብን ችግር በሳይንሳዊና ሀገር በቀል እውቀት ለመፍታት በጥናትና ምርምር ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው ብለዋል።

ይህንን  ለማሳካት የሚያስ፣ችል አሰራርና አደረጃጀት ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ  ገልጸዋል።

በፎረሙ መድረክ  ከ44 ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ምሁራን በሚቀርቡ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ በመምከር ላይ እንደሚገኙ የኢዜአ ሪፖርተር ከደብረብርሃን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም