በድሬዳዋ የጣለው ከባድ ዝናብና መብረቅ የአራት ሰዎችን ህይወት አጠፋ

57

ድሬዳዋ ፤ሚያዚያ 28/2013(ኢዜአ) በድሬዳዋ ከተማ ትናንት የጣለው ከባድ ዝናብና መብረቅ የአራት ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱን ፖሊስ አስታወቀ።

ባለፈው እሁድም በድሬዳዋ የጣላው ከባድ ዝናብ  የዘጠኝ ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱ ይታወሳል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን  የህዝብ ግንኙነትና የለውጥ ስራዎች ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ትናንት ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ለሁለት  ሰዓታት ያህል የጣለው ከባድ ዝናብ  በለገሃሬ ቀበሌ አንድ መኖሪያ ቤት አፍርሶ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የሶስት ህጻናት ህይወት አጥፍቷል።

በተጨማሪም በእናታቸውና ወንድማቸው ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶ በድል ጮራ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ  ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የጣላውን ዝናብ ተከትሎ በመልካ ጀብዱ ቀበሌ የወደቀ መብረቅ የአንድ ሰው ህይወት ሲያጠፋ ሌላ አንድ ሰው ጉዳት ደርሶበት ህክምና ላይ እንደሚገኝ  ኮማንደር ገመቹ  ገልጸዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር እና የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች አደጋው በደረሰበት የለገሀሬ ቀበሌ በመገኘት ተጎጂ ቤተሰቦችን አጽናንተዋል።

አቶ ከድር በወቅቱ እንዳሉት፤ በጋራና ተራራማ ስፍራ የሚኖሩ ለአደጋ የተጋለጡ ነዋሪዎችን ህይወት ለመታደግ ለጊዜው በቀበሌው ወጣት ማዕከል እንዲኖሩ ይደረጋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፤ ዝናብ እስከ ግንቦት መጨረሻ ሊቀጥል ስለሚችል የአደጋው ተጋላጮችን ለጊዜው ከአካባቢው በማንሳት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ለዚህም አንድ ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

በገሃሬ አደጋው በደረሰበት ስፍራ ከሚኖሩት ቤተሰቦች መካከል ወይዘሮ ከዲጃ አብዲ በሰጡት አስተያየት፤ አስተዳደሩ ለአካባቢው ነዋሪ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ቢፍቱ ሽምሸዲን በበኩላቸው፤አስተዳደሩ ለተፋሰስ የተሰሩ ክትሮች ሣይቀር በማፍረስ ህገ-ወጥ ግንባታ ጋራው ላይ የሚያካሄዱትን በማስቆም  ዘላቂ መፍትሄ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር  ባለፈው እሁድ  የጣላው ከባድ ዝናብ ባደረሰው አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም