ፕሬዘዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ለኒጀር ፕሬዘዳንት መሀመድ ባዙም ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔት ማብራሪያ ሰጡ

80

ሚያዚያ 28/2013 (ኢዜአ) ፕሬዘዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ለኒጀር ፕሬዘዳንት መሀመድ ባዙም ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔት ማብራሪያ ሰጡ::

ፕሬዘዳንቷ በኒጀር ርዕሰ መዲና ኒያሚ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል::

የፕሬዘዳንቷ ጉብኝት በቅርቡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን ለያዙት መሀመድ ባዙም እንኳን ደስ ያሎት ከማለት በተጨማሪ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ: በትግራይ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ: በኢትዮጵያና በሱዳን የድንበር ጉዳይ እና በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዙሪያ ማብራሪያ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተገልፇል::

በጉብኝቱ የተሳተፉት የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ን በተመልከተ ሰፊ ማብራርያ መስጠታቸው ተነግሯል::

ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የታዛቢዎችን ቡድን በመምራት በ19 93 እና በ1996 /እኤአ / በኒጀር የተደረጉ ፕሬዝደንታዊና ጠቅላላ ምርጫዎችን ታዝበዋል::

ኒጀርም በቅርቡ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማድረጓ ለአፍሪካ በጎ ምሳሌ እንደምትሆን ፕሬዘዳንቷ አስምረውበታል::

በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካን ከሚወክሉ ሶስት ሀገሮች መካከል ኒጀር አንዷ ናት::

ፕሬዘዳንት መሀመድ ባዙም በፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅም ሆነ በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ በተደረገላቸው ማብራሪያ ሰለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መልካም ግንዛቤ እንዳገኙ መግለጻቸውን የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም