በሰሜን አሜሪካ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የነበረን ቆይታ ስኬታማ ነው- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን አሜሪካ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የነበረን ቆይታ ስኬታማ ነው- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር
ሐምሌ 25/2010 የጥላቻን ግንብ አፍርሶ የፍቅር ድልድይ ለመስራት በሰሜን አሜሪካ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ጋር የነበራቸው ውይይት የተሳካ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ፡፡ የፍቅር ድልድይ የመስራትና የጥላቻ ግንብን የማፍረስ ሂደቱ ዋሽንግተን ዲሲ ተጀምሮ በሎስ አንለጀስ እና በሚኒሶታ የጥላቻ ግንቡ ፍርስራሽ መወገዱን ገልጸዋል። በሰሜን አሜሪካና ከካናዳ የመጡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ላደረጉላቸው አቀባበልና ለነበራቸው ቆይታም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የጥላቻ ግንቡ ፍርስራሽ ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ የፍቅር እና የአንድነት ድልድዩ በፅኑ መሰረት ላይ እንዲታነፅ የማድረግ ስራው በአቡነ መርቆርዮስ አዲስ አበባ መግባት መጀመሩንም ነው ያነሱት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስና ብፁዓን አባቶች ዛሬ ከጠላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር አዲስ አበባ ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሁለት ተከፋፍላ ከነበረበት ሁኔታ በመውጣት በእርቅ ወደ አንድነት በመምጣቷ ኩራትና ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል። የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ለሁለት የተከፈለች በመሆኑ በቀጣይ ወደ እርቅ መጥተው አንድ እንዲሆኑ ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን አሜሪካ በነበራቸው ቆይታ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራሮች ጋር በብዙ ጉዳዮች ላይ ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮችም በቅርቡ ወደ ሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማህብራዊ ጉዳዮች ላይ ለመታገልና ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸውልናል ነው ያሉት። ጃዋር መሃመድና ታማኝ በየነም ወደ ኢትዮጵያ በቅርቡ እንደሚመጡና ሀገራቸውን የማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከንግግር ባለፈ በተግባር ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ያረጋገጡበትና ወደ ሀገራቸው የመምጣት ፍላጎት እንዳላቸው ያንጸባረቁበት ጉብኝት እንደነበርም አንስተዋል። በመጪው መስከረም በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ወደ ሀገራቸው እንደሚመጡና የትራንሰፖርት፣ የሆቴልና ሌሎች አገልገሎት ሰጪ ተቋማት ከሚያተርፉት ገንዘብ በላይ ኢትዮጵያውያኑን በፍቅር እንዲያስተናግዱ ጥሪ አቅርበዋል።