የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስልጤ ዞን ቅርንጫፍ ለተቸገሩ 80 ሰዎች የምግብ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስልጤ ዞን ቅርንጫፍ ለተቸገሩ 80 ሰዎች የምግብ ድጋፍ አደረገ
ሆሳዕና፤ ሚያዚያ 27/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ስልጤ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለችግር ለተጋለጡ 80 ሰዎች የምግብ ድጋፍ አደረገ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሙሀባ ሁሴን እንደገለጹት፤ ድጋፉ የተደረገው ለአቅመ ደካማ አረጋውያንና ኤች አይ ቪ/ኤድስ በደማቸው ለሚገኝባችው ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ነው።
ድጋፉን ያደረጉት የረመዳን ፆምን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ጠቅሰው በዚህም ለ80 ሰዎች ለእያንዳንዳቸው 25 ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄት፣ ሁለት ሊትር የምግብ ዘይትና አንድ ኪሎ ግራም ቴምር የተከፋፈላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ የማማኒ ኤች አይ ቪ/ኤድስ በደማቸው ያለባቸው ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሙስጠፋ ወርቅቾ እንዳሉት፤ ማህበሩ አንድ ሺህ አራት መቶ አባላት አሉት።
የጤና ችግር ላለባቸው የማህበሩ አባላት በረመዳን የጾም ወቅት እንዳይቸገሩ ቀይ መስቀል ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል በወራቤ ከተማ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ወይዘሮ በህሬ ሽፋ በሰጡት አስተያየት፤ አቅመ ደካማና ሰርተው መብላት የማይችሉ በመሆናቸው በማፍጠሪያ ወቅት የምግብ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የተደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።