የጀግኖች ኢትዮጵያውን የአሸናፊነት ሚስጥር ለሀገራቸው የነበራቸው ፍቅር መሆኑን የአርበኞች ማህበር አባላት ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የጀግኖች ኢትዮጵያውን የአሸናፊነት ሚስጥር ለሀገራቸው የነበራቸው ፍቅር መሆኑን የአርበኞች ማህበር አባላት ገለጹ
ጅማ፤ ሚያዝያ 27/2013 (ኢዜአ) የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የአሸናፊነታቸው ሚስጥር አንድነት፣ ህብረታቸውና ለእናት ሀገራቸው የነበራቸው ፍቅር መሆኑን በጅማ ዞን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት ገለጹ፡፡
80ኛው የአርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የማህበሩ አባላት እንዳሉት፤ ኢትየጵያውያን አንድነታቸው ሲጠናከር ለጠላት ስጋት ናቸው።
ከአባላቱ መካከል አቶ ኢብሳ ባይሳ በሰጡት አስተያየት “እኛ አባት አርበኛች ሀገራችን ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ጠላትን ታግለን በማሸነፍ ወደመጣበት መልሰናል” ብለዋል፡፡
“ልጆቻችንም እንደኛ ውዲቷን ሀገራችንን በአንድነት መጠበቅ አለባቸው፤ ከኛ የበለጡ ሀገራቸውን የሚወዱና የሚጠብቁ እንዲሆኑ በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል” ሲሉም ገልጿል። ፡
በአምስት ዓመቱ የጠላት ጦርነት እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ኢብሳ የተማረው ወጣት ኢትዮጵያ በባዕድ ጠላት እንዳትደፈርና በባንዳዎች እንዳትጠቃ የአርበኛ ልጆች በመሆናቸው መንቃት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
ሌላው የማህበሩ አባል አቶ ኡርጌሳ ቄንሳ በበኩላቸው ፤ጠላት ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመን አባት አርበኞች ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሀገርን ማዳናቸውን አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጀግንነት በአለም የታወቀች በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን መውደድና መንከባከብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
አንድነትና ቆራጥነት ጠላትን ያስፈራል፣ ኢትየጵያውያን አንድነታቸው ሲጠናከር ጠላት ይሰጋል፤ ስለዚህ የአሁኑ ትውልድ በአንድነት መሰራት አለበት ያሉት ደግሞ የማህበሩ አባል ሻምበል ንጉሴ ገሰሰ ናቸው።
የኢትዮጵያ አናብስት የነጭ ወራሪን አፈር ከድሜ ያስጋጡት አንድ ሆነው በመቆማቸው ነው ያሉት ሻምበል ንጉሴ፤ ዛሬም ክፍተቱን መዝጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የአሸናፊነታቸው ሚስጥር አንድነትና ለሀገራቸው የነበራቸው ፍቅር በመሆኑ ወጣቱም ትውልድ ይህንን እንዲጠበቅ የማህበሩ አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡