ጋዜጠኞች ሀገርን የሚያሻግር የመገናኛ ብዙሃን ስራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል...ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ - ኢዜአ አማርኛ
ጋዜጠኞች ሀገርን የሚያሻግር የመገናኛ ብዙሃን ስራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል...ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ
አዳማ፤ ሚያዝያ 27/2013 (ኢዜአ) ጋዜጠኞች ሀገርን የሚያሻግር ሰዋዊ የሆነ የመገናኛ ብዙሃን ስራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስራ አመራር ቦርድ አባል ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አሳሰቡ።
በኢዜአ እና ሰላም ሚኒስቴር ትብብር በአዳማ ከተማ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ የተገኙት ዶክተር ቢቂላ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ጋዜጠኞች በሀገር ላይ የተቃጣውን አደጋ መቀልበስ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ በሙያቸው የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
የሙያ ስነ ምግባር በመላበስ ግጭትን ከማርገብ በመቆጠብ የዜጎች ሰላምና ደህንነትን በሚጠብቁ ዘገባዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ሀገርና ህዝብ እንዲቀጥሉ በማገዝ ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተጫወቱት የሰላም ጋዜጠኝነት ሚና የሚመሰገን ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ ፤ በተለይ በዘንድሮው ምርጫ ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ ያሉት ሂደቶች ለይተው በማወቅ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ማስቻል ከጋዜጠኞች የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል።
ለጥፋት የሚንቀሳቀሱ ሴረኞችን በማጋለጥ በምርጫ ዜጎች ህገ መንግስታዊ መብታቸውን የሚያረጋግጡበት መሆኑን ማስገንዘብ ከጋዜጠኞች እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በምርጫ ወቅት የህዝቦች ድምፅና ሰላም እንዲከበር ቅድሚያ በመስጠት መዘገብ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ሀገሪቱ ሽግግር ላይ መሆኗን ጋዜጠኞች በተገቢው በመገንዘብ ሳይንገጫገጩ ራሳቸውንና ሙያውን ጠብቀው ለህዝብ ሰላም አስቀድመው መስራት እንዳለባቸ ዶክተር ቢቂላ አሳስበዋል።
የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ተብለው የሚታመኑ ጭምር የሙያ መንገራገጭና በስሜት የመጠለፍ ዝንባሌዎች ውስጥ እንደገቡ ተመልክተናል ያሉት ዶክተር ቢቂላ ፤ጋዜጠኞች በውስጥና ውጭ ኢትዮጵያን ለመጉዳት የታቀደውን ሴራ በትብብር ለማክሸፍ ሙያዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
በአዳማ ከተማ ለጋዜጠኞች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ከመሆኑም ባለፈ ቀጣይ ሊኖር የሚችለውን ፈተናዎች በሙያዊ ስነ ምግባር ለማለፍ የሚያስችል ስንቅ የሚሆን ነው ብለዋል ።
ጋዜጠኞች ሀገርን የሚያሻግር ሰዋዊ የሆነ የመገናኛ ብዙሃን ስራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አመልክተው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ ያለው ሂደት ተሳክቶ ኢትዮጵያዊን እንዲያሸንፉ ተግተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።