ቀጥታ፡

ያለንበት ወቅት የውስጥና የውጭ ፈተና የተደቀነበት በመሆኑ በአንድነት መቆም ያስፈልጋል -ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 27/2013 (ኢዜአ) ያለንበት ወቅት የውስጥና የውጭ ፈተና የተደቀነበት በመሆኑ ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት መቆም፣ መከባባርና መተባበር ይጠይቃል ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባ ይህን የተናገሩት ዛሬ 80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል ቀን  በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት ነው። 

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወራሪው የኢጣሊያ ኃይል አድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈትና ያጣውን ድል ለመቀዳጀት አቅዶ ከ40 ዓመት በኋላ ተመልሶ ለወረራ መምጣቱን አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን ጀግኖች አርበኞቻችን የወራሪውን ከፋፍሎ የማጥቃት ስልት በሚገባ በመረዳታቸው በጀግንነት ተፋልመው ለድል መብቃታቸውን ተናግረዋል።

ይህ ድል ኢትዮጵያን የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ሆና እንድትጠቀስ ማስቻሉንም ምክትል ከንቲባዋ ጠቅሰዋል።

የአሁኑ ትውልድ ድሉን ተከትሎ አንገቱን ቀና አድርጎ በኩራት የሚኖርባት አገር እንድትኖረው ማስቻላቸውንም ተናግረዋል። 

ከጀግኖች አርበኞች መማር እና መውረስ ያለብን ድሉን ብቻ ሳይሆን ለድል ያበቃቸውን ስልት እና ማስተዋል ጭምር መሆኑንም ገልጸዋል።

ያለንበት ወቅት በአገሪቱ ላይ የውስጥና የውጭ ፈተና የተደቀነባት በመሆኑ ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት መቆምን፣ መከባባር እና መተባበርን ይጠይቃል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም