የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዓለም አቀፍ የአየር ጭነት ሽልማት አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዓለም አቀፍ የአየር ጭነት ሽልማት አገኘ

ሚያዚያ 27/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የ2021 ዓለም አቀፍ የአየር ጭነት ሽልማት አሸናፊ ሆነ።
ዓለም አቀፍ የአየር ጭነት ኢንዱስትሪ ጉባኤ "ኤር ካርጎ ኤሮፕ" እ.አ.አ በ2021 በ10 የአየር ጭነት አገልግሎት መስኮች አሸናፊ የሆኑ አየር መንገዶች እንዲሁም የካርጎና ጭነት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ዛሬ ባካሄደው የበይነ መረብ የሽልማት ስነ ስርዓት ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የካርጎና የሎጅስቲክ አገልግሎት የ2021 የአየር ጭነት ኢንዱስትሪ የደንበኞች እንክብካቤ ዘርፍ ሽልማት አግኝቷል።
መቀመጫውን በስዊዘርላንድ ያደረገው ዓለም አቀፍ የትራንስፖርትና የሎጅስቲክ ኩባንያ ኩኔ ኤንድ ናጌል የዓመቱ ምርጥ የአየር ጭነት አመላላሽ ዘርፍ ተሸላሚ ሆኗል።
የኳታር ኤርዌይስ የአየር ጭነት ስኬታማ ኢንዱስትሪ ዘርፍና የዓመቱ ምርጥ የካርጎ አየር መንገድ ሽልማቶችን አግኝቷል።
የሆላንዱ አምስተርዳም ሺፕሆል አየር መንገድ የዓመቱ ምርጥ አየር መንገድ ሽልማትን ያገኘ ሲሆን የስዊዘርላንዱ የአቪዬሽን አገልግሎት ኩባንያ ስዊዝፖርት የዓመቱ ምርጥ የካርጎ አገልግሎት ወኪል ድርጅት ዘርፍ ሽልማት ወስዷል።
ዓለም አቀፍ የአየር ጭነት ኢንዱስትሪ ጉባኤ "ኤር ካርጎ ኤሮፕ" በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ሽልማት በጀርመን ሙኒክ ከተማ ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የ2021 መርሃ ግብር በበይነ መረብ እንዲካሄድ መደረጉን አስታውቋል።
"ኤር ካርጎ ኤሮፕ" ዓመታዊ ሽልማቱን መስጠት የጀመረው እ.አ.አ በ2003 ነው።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ጊዜ የዓለም አገራት የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጣሏቸው የጉዞ ክልከላዎችና ገደቦች የአቪዬሽኑ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳርፏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ወረርሽኙ ያመጣውን ተጽእኖ ለመቋቋም የመንገደኞች ማጓጓዣ አውሮፕላኖችን ጭምር ወደ ካርጎ ጭነት አውሮፕላን በመቀየር የካርጎ ጭነት አገልግሎት ላይ በስፋት መሰማራቱ ይታወቃል።
በካርጎ ጭነት አገልግልት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውሉ የህክምና ግብአቶችን በዓለም ዙሪያ በማጓጓዝ አየር መንገዱ ወረርሽኙ ያስከትለው የነበረውን ጉዳት መቀነስ መቻሉን ሲገልጽ ቆይቷል።
በአሁኑ ሰዓት ደግሞ አየር መንገዱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባቶችን ወደተለያዩ ክፍለ ዓለማት እያጓጓዘ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ የካርጎ ጭነት እንደሚያጓጉዝ መረጃዎች ያመለክታሉ።