ወጣቱ ትውልድ ሃገሩን ከጠላት በመጠበቅ የአባቶቹን ገድል ሊደግም እንደሚገባ ጀግኖች አርበኞች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ትውልድ ሃገሩን ከጠላት በመጠበቅ የአባቶቹን ገድል ሊደግም እንደሚገባ ጀግኖች አርበኞች ተናገሩ
ጎንደር ፤ ሚያዚያ 27/2013 (ኢዜአ) የአንድነት መሰረቷ የጠነከረ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ወጣቱ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን የተጋድሎ ታሪክ በውል ተገንዝቦ ሀገሩን ከአጥፊዎች ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባ በጎንደር ከተማ የሚኖሩ ጀግኖች አርበኞች ተናገሩ፡፡
80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በጎንደር ከተማ መስቀል አደባባይ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ስነ-ስርዓት አባት አርበኛ ጥጋቡ ተስፋሁን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ወጣቱ ትውልድ ከታሪክ ወቀሳ ለመዳን የጀግኖች አባቶቹን የተጋድሎ ታሪክ በመድገም ከውጭና ውስጥ የገጠሙንን ጠላቶች በህብረትና በአንድነት በመሆን መመከት ይገባዋል ብለዋል።
ጀግኖች አርበኞች ክቡር ህይወታቸውን ገብረው ያቆዯትን አንዲት የተከበረች ኢትዮጵያ ወጣቱ ትውልድ በዘርና ሃይማኖት በመከፋፈል ሊያዳከሟት እንደማይገባ ነናግረዋል፡፡
''ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገጠማትን ፈተና ለመሻገር ወጣቱ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን ፈለግ በመከተል ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን በማጠናከር በህብረት ሊቆም ይገባል'' ያሉት ደግሞ አባት አርበኛ አደራጀው ለማ ናቸው፡፡
ጀግኖች አባቶች ኢትዮጵያን ሊያፈርስና ሊበታትን ከመጣ የውጭ ጠላት የታደጓት በብሄር፣ ሃይማኖትና ዘር ተከፋፍለው ሳይሆን ይልቁንም አንድ ሆነው በህብረት በመቆም በፈጸሙት አኩሪ የተጋድሎ ታሪክ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሴት አርበኛ ወርቄ ብሬ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ በታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጠላቶችዋ ዘንድ ታፍራና ተከብራ ለዘመናት የዘለቀቸው በትውልድ ቅብብሎሽ በተፈጸመ አኩሪ የጀግንነት ተጋድሎ በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ እንደ አባቶቹ በጽናት ሊቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የቅኝ ገዢዎችን ወረራር በመመከት በብቸኝነት ነጻነቷን አስጠብቃ የቆየችውን ኢትዮጵያን ዛሬም በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለማንበርከክ ላይ ታች የሚሉ ጠላቶቿን መክቶ ድል ለማድረግ ኢትዮጵያውን በአንድነት እንዲቆም አመልክተዋል፡፡
ጠንካራ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ወጣቱ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን አኩሪ የተጋድሎ በመገንዘብ ሀገሩን ከአጥፊዎች ሊጠብቅ እንደሚገባ ጀግኖች አርበኞቹ ተናግረዋል፡፡
ድል መታሰቢያ በዓሉ ስነ-ስርዓት የከተማው ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት ወጣቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡