ዳያስፖራው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል ... የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል ... የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮ በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ዳያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ለ"ገበታ ለአገር" ፕሮጀክትም 30 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ዳያስፖራው በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ድጋፉ የተሰበሰበው በቦንድ ሽያጭ፣ በስጦታና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህ በጀት ዓመት እስካሁን የተደረገው ድጋፍ ባለፈው በጀት ዓመት ከተሰበሰበው ገንዘብ ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለውም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ለግድቡ ግንባታ በአጠቃላይ 200 ሚሊዮን ብር ከዳያስፖራው ለመሰብሰብ መታቀዱንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በቅርቡ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ጋር ባደረገው ውይይት በዋሺንግተን ዲሲና አከባቢው የሚኖሩ ዜጎች ከ53 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንና 100 ሺህ ዶላር ለመስጠት ቃል መግባታቸውን አስታውሰዋል።
በተመሳሳይ በሚኒሶታና በሰሜን ማዕከላዊ የአሜሪካ ክፍል በሚገኙ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ የ40 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በዳያስፖራው ላይ ከፍተኛ መነቃቃትና ተነሳሽነት መፍጠሩንና ሙሌቱ አሁን እየተሰበሰበ ላለው ገንዘብ ያደረገው አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት ያስረዱት።
ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ያላትን አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስረዳት ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም ግብጽና ሱዳን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግድቡ ዙሪያ የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረው የሚያደርጉትን ዘመቻ በመመከት ሚዛናዊ እይታ እንዲኖር ከማድረግ አኳያ ውጤታማ ስራ እየሰሩ ይገኛል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ዳያስፖራው ለግድቡ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አማካኝነት ባለፈው ዓመት ይፋ በተደረገው የገበታ ለአገር ፕሮጀክት ዳያስፖራው እስካሁን 30 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም ነው ዋና ዳይሬክተሯ የገለጹት።
የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ማብቂያ ድረስ ከዳያስፖራው ለ"ገበታ ለአገር" ፕሮጀክት 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን አመልክተዋል።
የ"ገበታ ለአገር" ፕሮጀክቶችን ዳያስፖራው እንዲያውቀው ፕሮጀክቶቹን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና ዳያስፖራው ፕሮጀክቶቹን የመደገፍ ፍላጎት እንዳለውም ተናግረዋል።
ኮይሻ፣ጎርጎራንና ወንጪን ማልማት ዓላማ ያደረገው "ገበታ ለአገር" ፕሮጀክት ሶስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከሁለት ወራት በፊት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ዳያስፖራው ለአገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ወይዘሮ ሰላማዊት ጥሪ አቅርበዋል።