ምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲሳካ የድርሻውን እንደሚወጣ ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲሳካ የድርሻውን እንደሚወጣ ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ
ጅማ ፤ሚያዝያ 27/2013 (ኢዜአ) ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንደሚወጣ ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ።
ፓርቲው በጅማ ከተማ ዛሬ የጎዳና ላይ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሄዷል፡፡
በዚህ ወቅት የብልጽግና ፓርቲ የጅማ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አቶ ቲጃኒ ናስር እንደተናገሩት፤ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀገሪቱ ሠላማዊ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት ኖሮት በስኬት እንዲጠናቀቅ ብልጽግና ፓርቲ የበኩሉን ይወጣል።
በሁሉም ዘንድ ተዓማኒነት ያለውና ለምንገነባው የዴሞክራሲ ሂደት ፈር ቀዳጅ ምርጫ እንዲካሄድም እንዲሁ፡፡
አቶ ቲጃኒ ፤"ኢትዮጵያውያንን ለዘመናት በወንድማማችነት ያስተሳሰሩ የማንነት መገለጫዎች፣ ዓለምን ያስደመሙ ድንቅ እሴቶች፣ ባህልና ወጎች ያሉን ህዝቦች በመሆናችን አንድነት ያስፈልገናል" ብለዋል፡፡
ይህ ዓለም የሚመሰክረው ዘመናትን የተሻገረ የእኛ እውነት ነው፤ እነዚህን እሴቶች ይዘን ዛሬያችንን በማጽናት፤ ነገያችንን ደግሞ እንገነባለን ሲሉም አስታውቀዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ በጅማ ከተማ ያካሄደው የምረጡኝ ቅስቀሳ አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት "ወንድማማችነት የኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
ከከተማዋ ሁሉም ቀበሌዎች የተወጣጡ የፓርቲው ደጋፊዎች "ብልጽግና ያሻግረናል፤፤ ብልጽግና ሰላም ነው፤ ብልጽግና ልማትና ዴሞክራሲ ነው" የሚሉ መፈክሮችን አንግበው አደባባይ በመውጣት ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡