በገበታ ለሀገር ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በገበታ ለሀገር ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ
ሚያዝያ 27/2013 (ኢዜአ) በገበታ ለሀገር ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ፡፡
የዞኑ የመንግስት ሰራተኞች ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ግንባታ ድጋፍ እንዲውል ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ መለገሳቸው ተመልክቷል፡፡
በቦረና ዞን የያቤሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የመንግስት ሰራተኛ አቶ መንግስቱ እቲቻ በሰጡት አስተያየት የሀገራችንን እድገትና ልማት ለማፋጠን አንድነትንና ትብብርን ከማጠናከር ሌላ ምርጫ የለንም፡፡
ባለፉት ዓመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሶስት ዙር የ7 ሺህ 100 ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል፡፡
አሁን ደግሞ ከወር ደመወዛቸው ግማሹን በዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ ከ4 ሺህ ብር በላይ ለገበታ ለሀገር እንደለገሱ ገልጸዋል፡፡
ሌላው የመንግስት ሰራተኛ ወይዘሮ ኢያ ሚኦ ሙሉ በበኩላቸው የወር ደመወዛቸውን በዓመት ተከፍሎ እንዲያልቅ 11 ሺህ 636 ብር ለገበታ ለሀገር ማበርከታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ቀደም ሲልም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል በ9 ሺህ 800 ብር ቦንድ መግዛታቸው አስታውሰው፤ "አሁንም አጠናክሬ እቀጥልበታለሁ" ብለዋል፡፡
የቦረና ዞን ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት የበጀት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ መገርሳ መንገሻ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ከመንግስት ሰራተኞች 6 ሚሊዮን ብር ቃል መገባቱንም አስታውቀዋል፡፡
ልማቱን ለመደገፍ ቃል ከተገባው ገንዘብ ውስጥ እስካሁን 1 ሚሊዮን 258 ሺህ ብር ተሰብስቦ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኛው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመሩ ታላላቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ቡድን መሪው መልዕክት አስተላልፈዋል።