"ከጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን መውረስ ያለብን ድሉን ብቻ ሳይሆን የድላቸውን ጥበብ፣ ማስተዋል እና አንድነታቸውን ጭምር ነው"... ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
"ከጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን መውረስ ያለብን ድሉን ብቻ ሳይሆን የድላቸውን ጥበብ፣ ማስተዋል እና አንድነታቸውን ጭምር ነው"... ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ሚያዝያ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ)"ከጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን መውረስ ያለብን ድሉን ብቻ ሳይሆን የድላቸውን ጥበብ፣ ማስተዋል እና አንድነታቸውን ጭምር ነው "ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል።
በክብረ በአሉ ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት የኢጣሊያ ጦር የአድዋ ሽንፈቱን ለመመለስ በድጋሜ ያደረገውን ወረራ አባቶቻችን አይበገሬነታቸውን ዳግም ያስመሰከሩበት ታላቅ ድል ነው ብለዋል።
የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያ ለማሸነፍ ከጦርነት ባለፈ በዘር፣ በሀይማኖት እና በቋንቋም ጭምር ለበመታተን ያሴረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጀግኖች አባቶችና እናቶች ይህ ሴራ ሳይከፋፍላቸው በአንድነት ቆመው ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ እና የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት እንድትሆን አስችለዋል ብለዋል፡፡
የአሁኑ ትውልድም ከጀግኖች አርበኞች ማስተዋል እና ጥበብን በመማር በአንድነት በመቆም የተጋረጡትን አደጋ በመጋፈጥ የራሱን ታሪክ በመስራት ሊሆን እንደሚገባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
"ለጀግኖች አርበኞቻችን ክብር ይገባቸዋል" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ለጀግኖች አባቶችና እናቶች በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የከተማ አስተዳደሩ መወሰኑንም አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ለጠየቀው የገቢ ማስገኛ የመሬት ጥያቄ ከሊዝ ነጻ እንዲሰጠው መወሰኑንም ምክትል ከንቲባዋ አስታውቀዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የደረሰችው አባቶቻችን እና እናቶች በከፈሉት መሰዋእትነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"ይህንን ከአባት አያቶቻችን የወረስነውን አንድነት፣ አገር ወዳድነት እና አንዱ ለአንዱ መቆምን ጠብቀን ልናቆይ ይገባል" ማለታቸውን የከተማዋ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
80ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓል ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ጀግኖች አርበኞች እና ሌሎች የፌዴራልና የከተማዋ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ነው የተከብረው፡፡