ብልፅግና ፓርቲ በአዳማ ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ በአዳማ ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ አካሄደ
ሚያዚያ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ብልፅግና ፓርቲ በአዳማ ከተማ አባላትና ደጋፊዎቹ በተገኙበት የምርጫ ቅስቀሳ አካሄዷል።
በአዳማ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ቱሉ በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ብልጽግና ትክክለኛውን ፌዴራልዝም እውን በማድረግ ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅና የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ያለ ፓርቲ ነው።
"ብልፅግናን መምረጥ የሀገሪቱን የነገውን ተስፋ እውን ማድረግ ነው" ያሉት ሃላፊው፤ ፓርቲው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት እንዲሁም አብሮነት እንዲጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ሀገር በቀል የሆነ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን አንግቦ የተነሳ ፓርቲ መሆኑን አስረድተዋል።
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ አመኔታን ያተረፈ እንዲሆንም በሚካሄደው እንቅስቃሴ ፓርቲው የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ህዝቡ በካርዱ ለሀገር የሚበጀውን ብልፅግናን እንዲመርጥ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ሃይሉ ፤ብልፅግና ሀገሪቷን የፈተናትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት አዋጭ ፖሊሲ በማዘጋጀት ወደ ተግባር የገባ ፓርቲ መሆኑንም ተናግረዋል።
በከተሞች የዜጎች የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል እንዲሁም በገጠር የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ ወደ ተጨባጭ ስራ እየገባ ያለ ፓርቲ መሆኑንም አመልክተዋል።
ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሚበጀውን በመምረጥ ህገ መንግስታዊ መብቱን መጠቀም እንዳለበትም ተናግረዋል።
በስነ-ስርዓቱ ከታደሙት መካከል በአዳማ የገዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ መገርሳ ረጋሳ በሰጡት አስተያየት፤ ለሀገሪቱ የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርዱን ወስደን ቀኑን በመጠበቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ለሀገር አንድነት፣ ለህዝቦች እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማምጣት የሚበጀንን ፓርቲ እንመርጣለን ሲሉ ገልጸዋል።