“የኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነት መጠናከር የክብራችን ምንጭ እና የኩራታችን ጥግ ነው”…አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
“የኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነት መጠናከር የክብራችን ምንጭ እና የኩራታችን ጥግ ነው”…አቶ ደመቀ መኮንን
ሚያዝያ 27/2013(ኢዜአ) “የኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነት መጠናከር የክብራችን ምንጭ እና የኩራታችን ጥግ መሆኑን በውል በመረዳት፤ በሁሉም የለውጥ እና የእድገት መስመሮች እያበርን ኢትዮጵያን ማሻገር ይጠበቅብናል” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ዛሬ ለሚከበረው 80ኛ ዓመት የዐርበኞች የድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ደመቀ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ካለችበት አሁናዊ ሁኔታ አንፃር ከመቼውም ጊዜ በላይ የቀደሙ አባቶቻችን የአርበኝነት ወኔ እና አበርክቶ በዚህ ትውልድ መድገም የሚጠይቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።
አሁን የተገባበት ትግል ሃገር ለማፍረስ እና ሃገር ለማቆም በሚደክሙ ሃይላት መካከል የሚካሄድ በመሆኑ፤ አፍራሽ ሃይሎች አቅም እና ጊዜ እንዳይገዙ ትውልዱ ሃገርን በማዳን ተልእኮ ውስጥ የአርበኝነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ከውስጥ እና ከውጭ በሀገሪቱ የተደቀኑ ፈተናዎች በድል እና በስኬት ለመሻገር፤ የውስጥ ልዩነቶች ወደኋላ ሳይጎትተው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት እና በጋራ ሊቆም እንደሚገባም ገልጸዋል።
“ሁላችንም እንደምንገነዘበው እስካሁን አንድነታችን ፀንቶ በማበራችን በርካታ መሰናክሎችን ተሻግረናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “በቀጣይ ህብረታችን ጠብቆ ትውልድ እና ሃገር በሚያሻግሩ ተግባራት ላይ እንድንረባረብ አደራ ለማለት እወዳለሁ” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።