ቀጥታ፡

የጋዜጠኝነት ሙያ ከፖለቲካውና ማህበረሰብ አንቂው ጋር መደባለቅ ለጥላቻ ንግግር መስፋፋት ምክንያት መሆኑ ተገለጸ

ሚያዚያ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ከፖለቲካውና ማህበረሰብ አንቂው ጋር እየተደባለቀ መምጣቱ ለጥላቻ ንግግር መስፋፋት መንስኤ መሆኑ ተነገረ። የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የወቅቱ ፈተናዎች ናቸውም ተብሏል።
30ኛው የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን "መረጃ ለሕዝብ ጥቅም" በሚል መሪ ቃል ዛሬ ተከብሯል።

የበዓሉ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና ባህል ተቋም(ዬኔስኮ) እና አጋር አካላት ትብብር የተዘጋጀ ነው።

ቀኑን አስመልክቶ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የጋዜጠኝነት ሙያ ከፖለቲካውና ማህበረሰብ አንቂው ጋር መምታታቱ የጥላቻ ንግግር እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

ፖለቲከኞችና ማህበረሰብ አንቂ የሚባሉ ሰዎች በመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ የሚሰጧቸው አስተያየቶች በሕዝብ መሐል ቅራኔ እየፈጠሩ መምጣታቸውን ተመልክቷል።

እነዚህ አካላት የሚያገኟቸው መገናኛ ብዙሃን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መቃቃርና አለመግባባት የሚፈጥሩ መልዕክቶችን እንደሚያንጻባርቁ ነው በውይይቱ ወቅት የተነሳው።

ወገናዊነትና ግጭትን የሚቀሰቅሱ ሀሳቦችን በመገናኛ ብዙሃን የሚያስተላልፉ ሰዎችን እንደ ጋዜጠኛ የማየት ዝንባሌ እየታየ እንደሚገኝና ይሄ አመለካከት ሊስተካከል እንደሚገባው ተገልጿል።

ጋዜጠኝነት ከማህበረሰብ አንቂነትና ፖለቲካው መስክ የተለየ ራሱን የቻለ የሙያ ዘርፍ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።

በተለይም በማህበራዊ ትስስር ገጾች አማካኝነት እያንዳንዱ መልዕክት አስተላላፊ "ጋዜጠኛ" እየሆነ መምጣቱንና ይሄም ለመገናኛ ብዙሃን ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ተጠቅሷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ዩሚኮ ዮኮዜኪ በበኩላቸው የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ የወቅቱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የወቅቱ ፈተናዎች ናቸው ብለዋል።

መንግስትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ያደረገቻቸው ማሻሻያዎች የሚበረታቱ እንደሆኑና ዩኔስኮ በዘርፉ ለሚከናወኑ ማሻሻያዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተወካይ ዶክተር ሄኖክ ስዩም መገናኛ ብዙሃን ለማህበረተሰቡ የሚያደርሷቸው መረጃዎች ለሕዝብ የሚጠቅሙ እንጂ የሚጎዱ መሆን የለባቸውም ብለዋል።

በዚህ ረገድም መገናኛ ብዙሃን ሕብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃዎችን የማድረስ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው በመገናኛ ብዙሃን ዙሪያ የወጡ ህጎችን አለማክበር፣ ሚዛናዊነት የጎደላቸው መረጃዎችን ማቅረብ፣ የአገርን ብሄራዊ ጥቅም ከሚያስጠብቁ መረጃዎች ይልቅ ብሄርን ከብሄርና፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ መረጃዎች በመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መገናኛ ብዙሃንና የሚመለከታቸው አካላት በኃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

በ30ኛው የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን አከባበር ላይ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የዘርፉ ምሁራንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም