ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎቹን ለህዝብ አስተዋወቀ

ሀዋሳ ሚያዚያ 26/2013 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀዋሳ ከተማ ለህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ዕጩዎቹን ዛሬ ለህዝብ አስተዋወቀ።

በአስተዳደሩ ፓርቲውን በመወከል ለህዝብ ተወካዮችና ለሲዳማ ክልል ምክር ቤቶች  ለመወዳደር 11 ዕጩዎች ቀርበው ለህዝቡ የማስተዋወቅ ፕሮግራም ተካሄዷል።

ከመካከላቸውም  የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ  አቶ ጥራቱ በየነ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ብቸኛው ዕጩ እንደሆኑ ተመልክቷል።

የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤቱ የሀዋሳ ከተማ  አስተዳደር ሃላፊ  አቶ ካሱ አሩሶ  በትውውቅ  ስነ-ስርዓት እንዳሉት፤ ዕጩዎቹ ለምርጫው  እንዲወዳደሩ  ፓርቲው  ያቀረባቸው በትምህርት ዝግጅት፣ በተሰማሩባቸው የስራ መሰኮች ውጤታማነት፣ በመልካም ስነምግባራቸውና በህዝብ ዘንድ ባላቸው ተቀባይነት ተመርጠው ነው።

ከዚህ ባለፈው ዕጩዎቹ  ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተውጣጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ፓርቲው በምርጫው ካሸነፈ የከተማዋን ዕድገትና  የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

በፓርቲው የከተማዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በበኩላቸው ፓርቲው በሚከተለው ህብረ ብሄራዊ ፌዴራልዝም ስርዓት የህዝቦች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በማሳደግ ብልጽግናን ለማምጣት ዕጩዎቹ ትልቅ አቅም አላቸው ብለዋል።

በከተማዋ የሚኖሩ ህዝቦችን ኑሮ ለማሻሻልና አዳዲስ የልማት ስራዎችን በማከናወን ወደ ተግባር መለወጥ እንዲቻል የሀዋሳ ነዋሪዎች ለብልጽግና ያላቸውን ድጋፍ በምርጫውም እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።

የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪ አቶ ጥራቱ በየነ እንደገለጹት፤ ብልጽግና በምርጫው ካሸነፈ  ለወከላቸው የሀዋሳ ከተማና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅሙ ተግባራት በብቃት፣ በታማኝነትና በቅንነት ለመስራት ዝግጁ ናቸው።

በትውውቅ ስነ-ስርዓቱ የተገኙት በሀዋሳ የባህል አዳራሽ ክፍለ ከተማ ነዋሪ   አቶ ማርቆስ  ኤልያስ በሰጡት አስተያየት፤ የዕጩዎች ምርጫና የምልመላ መስፈርት አስደስቶኛል  ብለዋል።

በቀረቡት ዕጩዎች ውስጥ የምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ ብሄረሰቦች  ተዋጽኦ  ያለበት መሆኑ የፓርቲውን ፍትሀዊነት ያሳያል ብለዋል።

ዕጩዎቹ  ምርጫው ሰላማዊና ተአማኒ  ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን  ለመወጣት  ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲን በመወከል በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በዕጩነት ለመወዳደር  ከቀረቡት መካከል አራት ሴቶች እንደሚገኙበት ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም