ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ለታላቁ የ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ19 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

ባህርዳር፤ ሚያዚያ26/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥ ከ19 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መድረጉን የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ላቀ ጥላዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የግድቡ ግንባታ የሚካሄደው  በራስ አቅም በመሆኑ መንግስትና ህዝቡ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።

በአማራ ክልልም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ19 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ በቦንድ ግዥ በማሰባሰብ ለግድቡ ግንባታ እንዲውል ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

በዚህም የመንግስት ሰራተኞች ከወር ደመወዛቸውንና ጡረተኞችም ግድቡ  እስኪጠናቀቅ ከሚያገኙት የጡረታ ገቢ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸው በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በጸጥታ ፣በኮሮና በሽታና ሌሎች ምክንያቶች ህዝቡ ችግር ውስጥ ቢሆንም ለህዳሴው ግድብ የሚያደርገው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን አስረድተዋል።

የህዳሴው ግድብን ከደለል ነጻ ለማድረግም በተፋሰሱ ዞኖችና ወረዳዎች የሚገኘው ህዝብ ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ 26 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሚገመት ነጻ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በማከናወኑ በጉልበቱ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አውስተዋል።

በየዓመቱ የሚካሄደው የአፈርና ውሃ እቀባ ስራም የአካባቢውን የአፈር መሸርሸር በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የህዳሴው ግድብ በደለል ከመሞላት ለመታደግና የውሃ ፍሰቱን ለመጨመር ማገዙን አስረድተዋል።

የሚካሄደውን የተፈጥሮ ሃብት ልማት በሳይንሳዊ እውቀትና ክህሎት ለመደገፍ የደብረ ማርቆስ፣ ባህር ዳር፣ ወሎ፣ አሶሳና ሌሎች በተፋሰሱ  የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች  በምርምር  የታገዘ ወርክ ሾፕ እያካሄዱ ይገኛሉ ብለዋል።

በሀገር ውስጥና ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞች የአባይ ግድብን ፍትሃዊነት አስመልክቶ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በመከራከርና በመሞገት የዜግነት ዲፕሎማሲው ከምን ጊዜውም በላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ  ማድረስ መቻላቸውንም ጠቅሰዋል።

ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ደራስያን፣ ሙዚቀኞችና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሙያተኞች በተለያዩ ቋንቋዎች ባበረከቱት አስተዋጽኦ የግብጽና መሰሎቿ የዘመናት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እየተናደ መምጣቱን አመላክተዋል።

አሁን ላይ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆኑ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሞት ሽረት ሴራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ከ79 በመቶ በላይ የደረሰውን የግድብ ግንባታ በስኬት ለማጠናቀቅም መላው ኢትዮጵዊያን የጠላቶቻችን ሴራ ለማክሸፍ በአንድነትና በቁርጠኝነት መረባረብ አለብን ብለዋል።

የህደሴው ግድብ ግንባታ በመላው ኢትዮጰያውያን የገንዝብ፣ ጉልበትና እውቀት አስተዋጽኦ የተገነባ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው የጠቀሱት አቶ ላቀ ፤ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሳ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ የአማራ ክልል ህዝብ በጉልበትና ገንዘብ ያደረገውን አስተዋጽኦ ከ30 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ማድረሱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም