ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል -- የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

ሚያዚያ 26/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው የተነሱባት አገር በመሆኗ ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

የባህር ኃይል አርማ፣ የትከሻ ምልክትና የደንብ ልብስ ዛሬ ቢሾፍቱ በሚገኘው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ይፋ ሆኗል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ የባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ እና ጥሪ የተደረገላቸው የውጭ አገራት አታሼዎችና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የመሰረታዊ ባህረኞች ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ቢሾፍቱ በሚገኘው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ በማኖር፤ ለባህር ኃይል የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ጠንካራ ባህር ኃይል የነበራት አገር እንደነበረች አስታውሰው "የኢትዮጵያ ሰራዊት የደርግ ሰራዊት ነው በሚል እንዲፈርስ በተደረገ ጊዜ ባህር ኃይሉም አብሮ ፈርሷል" ብለዋል።

ውሳኔው በኢትዮጵያ ታሪክ አሳዛኝና አሳፋሪ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ጄኔራል ብርሃኑ ይህ መሆኑ በአሁኑ ወቅት አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ስለመሆኑ ነው ያብራሩት።

ኢትዮጵያ ለቀይ ባህርና ህንድ ውቂያኖስ ባላት ቅርበት በዚያ የሚመጣ አደጋ ሊያጠቃት እንደሚችል ነው የገለጹት።

አሁን ያለው መንግስት ይህን ውሳኔ በመቀልበስ ባህር ኃይል መልሶ እንዲቋቋም በማድረጉ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሰው ኃይልና ባለሙያ ግንባታ ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ነው ያወሱት።

ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ግንባር ፈጥረው የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ እነዚህ ጠላቶች አገሪቷን በማዳከም ከችግር እንዳትወጣ፣ ታላቅነቷን አስጠብቃ እንዳትሄድ እየሰሩ ነው ብለዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የሚፈጠሩትን ግጭቶች ሰራዊቱ በየቦታው እየሄደ እያመከነ ይገኛል ነው ያሉት።      

ይህ ሁሉ ትንኮሳ፣ ማናቆርና ህብረተሰቡን እርስበርሱ ማባላትና ኢትዮጵያን ለማዳከም ያለመ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ፍላጎቱም አገሪቱ ስትዳከም ባላት ሃብት እንዳትጠቀም ማድረግ ነው ብለዋል።

ከ100 ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ኃይሎች ዛሬ ተጠናክረው አገራችን ላይ ዘምተዋል ብለዋል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ።

"አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉት እነዚህን ኃይሎች በውጭ ወራሪ እንደማንቻል ስለሚያውቁ ከውስጣችን ባንዳዎችን ይዘው ሊያፈራርሱን ያስባሉ" ነው ያሉት።

ህዝቡ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም የተደገሰውን ለማክሸፍ መታገል ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።

"ኢትዮጵያን ለማዳን ሁላችንም አንድ መሆን ይገባናል፤ ተሳስተው የጠላት መሳሪያ የሆኑ አካላትም ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል፤ ለአገራቸው ጥፋት እየደገሱ ለሌሎች ታሪካዊ ጠላቶች በር መክፈት የለባቸውም" ብለዋል።

ሰራዊቱም ኢትዮጵያን ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰለፍ፤ ኢትዮጵያም ይህን ችግር በመሻገር ወደፊት እንደምትራመድ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡም ኢትዮጵያን ለመጠበቅና ከውጭ ወራሪዎች ለመከላከል አንድ ሆኖ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

የባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ በበኩላቸው ባህር ኃይል በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኃይሉን እንደገና ለማደራጀት የሚያስችሉ ቁልፍ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን አውስተዋል።

የሰው ኃይል አቅምን መገንባት የሚያስችል መሰረታዊ ባህረኞች ማሰልጠኛ ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መጣል፣ አርማ፣ የትከሻ ምልክትና የደንብ ልብስ የዚሁ አካል መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባህር ኃይልን እንደገና የመገንባት ስራ ትልቅ ኃብትና ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት ደረጃ በደረጃ በመገንባት ወደ ለውጥ ለመሸጋገር መሰረት የሚጥል ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።

በለውጡ የባህር ኃይልን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሰረት ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ጥቅሞች ላይ ከባህር ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን በብቃት የመመከት ራዕይ አንግቦ እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም